ትንቢተ ሕዝቅኤል 3
3
1 #
ራእ. 10፥9፤10። እርሱም እንንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የቀረበልኽን ብላ፥ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር። 2አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ። 3እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።
4እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ንገራቸው። 5ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ ሕዝብ አልተላክህምና፥ 6ንግግራቸው ጥልቅ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ፥ ቃላቸውንም መስማት ወደማይቻልህ ታላላቅ ሕዝቦች አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ ይሰሙህ ነበር። 7ነገር ግን የእስራኤል ቤት እኔን መስማት እንቢ ብለዋልና አንተንም አይሰሙህም፥ ምክንያቱም የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና። 8እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ። 9ግምባርህን ከባልጩት እንደሚጠነክር አልማዝ አድርጌዋለሁ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አትፍራቸው፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ።
10እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ያዝ፥ በጆሮህም ስማ። 11ተነሥተህም ወደ ተማረኩት፥ ወደ ሕዝብህ ልጆች ሂድ፥ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው።
ሕዝቅኤል በኮቦር ወንዝ
12መንፈስም አነሣኝ፥ ከኋላዬም የጌታ ክብር ከሥፍራው ይባረክ የሚል ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ሰማሁ። 13ይህም የሕያዋኑ ክንፎች እርስ በእርሳቸው ሲማቱ የሚወጣው ድምፅ፥ በአጠገባቸውም የነበሩት የመንኰራኵሮች ድምፅ ነበር፥ እርሱም ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ነበር። 14መንፈስ አነሳኝ፥ ወሰደኝም፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቁጣ ሄድሁ፥ የጌታም እጅ በላዬ ላይ በርትታ ነበር። 15በኮቦር ወንዝ አጠገብ ወደሚኖሩ፥ በቴልአቢብም ወዳሉ ምርኮኞች መጣሁ፥ በዚያ በሚኖሩበትም ሰባት ቀን በመካከላቸው በድንጋጤ ተቀመጥሁ።
16ከሰባቱም ቀን በኋላ የጌታ ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እንዲህም አለኝ፦ 17የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፥ የአፌን ቃል በሰማህ ጊዜ ታስጠነቅቅልኛለህ። 18እኔ ኃጢአተኛውን፦ ሞትን ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ ካላስጠነቀቅኸው፥ ከክፉ መንገዱ እንዲመለስ ኃጢአተኛውን አስጠንቅቀህ ካልነገርኸው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 19ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው፥ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ እርሱ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። 20ጻድቁ ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት ከሠራ፥ እኔም በፊቱ ዕንቅፋትን አደርጋለሁ፥ እርሱም ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል፥ የጽድቁም ሥራ አይታሰብለትም፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 21ነገር ግን ጻድቁን ኃጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀው፥ ጻድቁም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፥ አንተም ነፍስህን አድነሃል።
የሕዝቅኤል መገለልና ዝም ማለት
22በዚያም የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ተነሥ፥ ወደ ሜዳ ውጣ፥ በዚያም ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ። 23እኔም ተነሥቼ ወደ ሜዳው ወጣሁ፥ እነሆ በዚያ በኮቦር ወንዝ ያየሁትን ክብር የሚመስል የጌታ ክብር ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ። 24መንፈስም ገባብኝ፥ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ፦ ሂድ፥ በቤትህ ውስጥ ዘግተህ ተቀመጥ። 25አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ ገመድ ያደርጉብሃል፥ ከእነሱም ጋር ያስሩሃል፥ ከመካከላቸውም አትወጣም፤ 26ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ፥ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚገስጽ ሰው አትሆንባቸውም። 27ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ