ትንቢተ ሕዝቅኤል 3

3
1እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ያገኘኸውን ብላ፥ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ። 2አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ። 3እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።
4እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ተናገራቸው። 5ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፥ 6ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር። 7ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙም። 8እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ። 9ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑ አትፍራቸው፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ።
10እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ተቀበል በጆሮህም ስማ። 11ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፥ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው አለኝ።
12መንፈስም አነሣኝ፥ በኋላዬም፦ የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ የሚል የጽኑ ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ። 13የአራቱም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የጽኑውንም ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ። 14መንፈስ አንሥቶ አስወገደኝ፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፥ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር። 15በቴልአቢብም ወዳሉ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፥ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፥ በዚያም ሰባት ቀን በድንጋጤ በመካከላቸው ተቀመጥሁ።
16ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 17የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፥ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 18እኔ ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 19ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። 20ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱም ዕንቅፋትን ሳደርግ፥ እርሱ ይሞታል፥ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል ያደረጋትም ጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 21ነገር ግን ኃጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብታስጠነቅቅ እርሱም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፥ አንተም ነፍስህን አድነሃል።
22በዚያም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም፦ ተነሥተህ ወደ ቈላው ሂድ በዚያም እናገርሃለሁ አለኝ። 23እኔም ተነሥቼ ወደ ቈላው ሄድሁ፥ እነሆም፥ በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ክብር ያለ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ። 24መንፈስም ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ፦ ሂድ፥ ገብተህ ቤትህን ዝጋ። 25አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ ገመድ ያደርጉብሃል ያስሩህማል፥ አንተም በመካከላቸው አትወጣም፥ 26እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም። 27ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ ትላቸዋለህ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ