የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 3

3
1እግዚአብሔርም “የሰው ልጅ ሆይ! የቀረበልህን ብላ፥ ይህን የብራና ጥቅል ብላ፤ ወደ እስራኤልም ሕዝብ ሄደህ ተናገር!” አለኝ።
2ስለዚህ አፌን ከፈትኩ፤ የብራናውንም ጥቅል እንድበላው ሰጠኝ፤ 3“የሰው ልጅ ሆይ! ይህን የሰጠሁህን የብራና ጥቅል ብላው! ሆድህንም በእርሱ ሙላው!” አለኝ፤ እኔም በበላሁት ጊዜ ጣፋጭነቱ እንደ ማር. ነበር። #ራዕ. 10፥9-10።
4ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄደህ እኔ የምነግርህን ቃል ንገራቸው፤ 5እኔ የምልክህ ወደ እስራኤላውያን እንጂ ቋንቋቸው ወደማይታወቅ ባዕዳን ሕዝብ አይደለም፤ 6ንግግራቸው ግራ የሚያጋባ፥ ቋንቋቸው ወደማይታወቅና የቃላቸውን ትርጒም ልታስተውለው ወደማትችል ታላላቅ ሕዝቦች ልኬህ ቢሆን ኖሮማ በሰሙህ ነበር። 7ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለ ሆኑ እኔን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ አንተንም አይሰሙህም። 8እኔ ግን አንተን እንደ እነርሱ እልኸኛና የማትበገር አደርግሃለሁ። 9አንዳችም የሚገታህ ነገር እስከማይኖር ድረስ መልእክቴን ለመናገር ቈራጥ ትሆናለህ፤ አንተን ይበልጥ ያጠነከርኩህ ስለ ሆነ እነዚህን በዕብሪት ዐመፀኞች የሆኑትን የምትፈራበት ምንም ምክንያት የለም።”
10ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የምናገረውን ሁሉ በጥንቃቄ አድምጠህ አስብበት። 11በምርኮ ወደሚገኙት የአገርህ ሕዝብ ሄደህ ቢሰሙህም ባይሰሙህም እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ ንገራቸው።”
12ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አደረገኝ፤ ከበስተኋላዬም “በሰማይ ለሚኖር እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ይሁን!” የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። 13የሕያዋን ፍጥረቶቹ ክንፎቹ እርስ በርሳቸው በአየር ላይ ሲፋጩ ሰማሁ፤ ከመንኰራኲሮቹም የሚሰማው የጋጋታ ድምፅ ከፍተኛ ነበር። 14መንፈስ አንሥቶ በወሰደኝ ጊዜ ስሜቴ በምሬትና በቊጣ ተሞልቶ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ኀይል በእኔ ላይ በርትቶ ነበር። 15ስለዚህ በኬባር ወንዝ አጠገብ ወዳለው ወደ ቴል አቢብ መጣሁ፤ ይህም ስፍራ የምርኮኞች መኖሪያ ነበር፤ ባየሁትና በሰማሁት ነገር ሁሉ በመደንገጥ ደንዝዤ በመካከላቸው ሰባት ቀን ቈየሁ።
እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን እረኛ አድርጎ እንደ ሾመው
(ሕዝ. 33፥1-9)
16ሰባቱ ቀኖች ካለፉ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 17“የሰው ልጅ ሆይ! እኔ ለእስራኤል ሕዝብ ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን ቃል ስማ፤ የምሰጥህንም የማስጠንቀቂያ ቃል ንገራቸው። 18እኔ አንድን በደለኛ በኃጢአቱ ምክንያት በእርግጥ ትሞታለህ ብለው አንተ ግን ያን ሰው ከኃጢአቱ ተመልሶ ይድን ዘንድ ባታስጠነቅቀው እርሱ በኃጢአቱ ይሞታል፤ ስለ እርሱ ሞት ግን አንተን ተጠያቂ አደርግሃለሁ። 19ኃጢአተኛውን አስጠንቅቀኸው፥ ከኃጢአቱ ባይመለስ እርሱ በኃጢአተኛነቱ ይሞታል፤ አንተም በኀላፊነት ከመጠየቅ ራስህን ታድናለህ።
20“በደግነቱ የታወቀ ጻድቅ ሰው ክፉ ሥራ መሥራት ቢጀምርና እኔም በችግር ላይ እንዲወድቅ ባደርገው፥ አንተ ካላስጠነቀቅኸው በቀር በኃጢአቱ ይሞታል፤ ከዚያ በፊት የፈጸመው መልካም ሥራ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ስለ እርሱ ሞት አንተን በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ። 21በደግነቱ የታወቀ ጻድቅ ሰው ኃጢአት ከመሥራት እንዲገታ ብታስጠነቅቀውና የአንተን ማስጠንቀቂያ ተቀብሎ ኃጢአት ከመሥራት ቢቈጠብ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም በኀላፊነት ከመጠየቅ ራስህን ታድናለህ።”
የሕዝቅኤል አንደበት መተሳሰር
22ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ኀይል በእኔ ላይ ነበረ፤ “ተነሥተህ ወደ ሸለቆ ሂድ፤ በዚያም አነጋግርሃለሁ” አለኝ።
23ስለዚህ ተነሥቼ ወደ ሸለቆው ወረድኩ፤ እዚያም በኬባር ወንዝ አጠገብ ባየሁት ሁኔታ የእግዚአብሔር ክብር ተገለጠልኝ፤ በግንባሬም ወደ መሬት ተደፋሁ፤ 24ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እኔ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “ወደ ቤትህ ሂድ፤ በርህንም ዘግተህ ተቀመጥ። 25የሰው ልጅ ሆይ! በገመድ ስለምትታሰር ወደ አደባባይ መውጣት አትችልም፤ 26ይህን ዐመፀኛ ሕዝብ ማስጠንቀቅ እንዳትችል አንደበትህ እንዲተሳሰር አደርገዋለሁ፤” 27ዳግመኛ ስናገርህና አንደበትህን ስከፍትልህ እንዲህ ትላቸዋለህ፦ “ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እነርሱ ዐመፀኞች ስለ ሆኑ ለመስማት የሚፈቅዱ ይስሙ፥ ለመስማት የማይፈቅዱ ይተዉት።’ ”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ