የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 4

4
ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን በጠላት መከበብ በምሳሌ ማስረዳቱ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! አንድ ጡብ ወስደህ በፊትህ አኑር፤ በላዩም ላይ የኢየሩሳሌምን ከተማ የሚያመለክት ካርታ ንደፍበት። 2ልክ እንደ አንድ ከተማ አስመስለህ በጡቡ ላይ አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ፤ እስከ ጫፍ ድረስ የዐፈር ቊልልና መወጣጫ ሠርተህ ጡቡን በጠላት ወታደር እንደሚከበብ አስመስለህ ክበባት። በሁሉም አቅጣጫ የእንጨት ምሰሶ ሠርተህ የከተማይቱን የቅጥር በር የምታፈርስ አስመስል። 3የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማይቱ መካከል እንደ ቅጽር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ ከተማይቱ አቅና፤ የተከበበችም ትምሰል፤ የምትከባትም አንተው ነህ፤ ይህም ለእስራኤል ሕዝብ ምልክት ይሆናል።
4“እንግዲህ በግራ ጐንህ ተኝተህ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ተሸከም፤ በጐንህ በምትተኛባቸው ቀኖች ቊጥር የእነርሱን ኃጢአት ትሸከማለህ። 5እስራኤላውያን ኃጢአት በሠሩባቸው ዓመቶች ብዛት ቀኖችን መድቤልሃለሁ፤ ይህም አንድ ቀን ለአንድ ዓመት ማለት ነው፤ ስለዚህ ለሦስት መቶ ዘጠና ቀኖች የእስራኤላውያንን ኃጢአት ትሸከማለህ። 6ያንንም ከፈጸምክ በኋላ ተዛውረህ በቀኝ ጐንህ በመተኛት እንደገና የይሁዳን በደል አርባ ቀን ትሸከማለህ፤ ይህም እነርሱን በምቀጣበት በእያንዳንዱ ዓመት ልክ ይሆናል ማለት ነው።
7“ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ትኲር ብለህ ተመልከት፤ እጅህንም አንሥተህ የማስጠንቀቂያ ትንቢት በእርስዋ ላይ ተናገር። 8ከበባው እስኪፈጸም ድረስ ከአንድ ጐንህ ወደ ሌላው እንዳትዘዋወር በገመድ አስርሃለሁ።
9“አሁንም ስንዴና ገብስ፥ ባቄላና ምስር፥ ማሽላና ጠመዥ ውሰድ፤ ሁሉንም በአንድነት ደባልቀህ እንጀራ ጋግር፤ ይህም በግራ ጐንህ በምትተኛባቸው በ 390 ቀኖች ውስጥ የምትመገበው ነው። 10በየቀኑ 230 ግራም የሚመዝን ምግብ ትወስዳለህ፤ እርሱም እስከሚቀጥለው ቀን እንዲበቃህ በማድረግ በተወሰነ ሰዓት ትመገበዋለህ። 11የምትጠጣውም ውሃ የተመጠነ መሆን ስለሚገባው በቀን ሁለት ኩባያ ብቻ ትጠጣለህ። 12የደረቀውን የሰው ዐይነ ምድር በማገዶነት ተጠቅመህ ሰው ሁሉ አንተን በሚያይበት ስፍራ እንደ ገብስ እንጀራ ጋግረህ ትመገበዋለህ።”
13እግዚአብሔርም፦ “ይህም እስራኤላውያንን በባዕድ አገሮች ሁሉ በምበትናቸው ጊዜ በሕግ የተከለከሉትን የረከሱ ምግቦች የሚመገቡ መሆናቸውን ያመለክታል” አለ።
14እኔም እንዲህ ስል መለስኩ፦ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ይህስ ከቶ አይሁን! እኔ ከቶ ረክሼ አላውቅም፤ ከሕፃንነቴ ጀምሮ የበከተ ወይም አውሬ የገደለው ከብትን ሥጋ የበላሁበት ጊዜ የለም፤ ጸያፍ ምግብም አልበላሁም።”
15እግዚአብሔርም “መልካም ነው፤ እንግዲያውስ በሰው ዐይነ ምድር ፈንታ የእንስሶችን ኩበት ወስደህ እርሱን በማቀጣጠል እንጀራ ጋግር” አለኝ።
16ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለኢየሩሳሌም የሚቀርበው ምግብ ሁሉ እንዲቋረጥ አደርጋለሁ፤ በዚያ የሚኖሩ ሕዝብ በፍርሃትና በስጋት ተሞልተው የሚበሉትን እህልና የሚጠጡትን ውሃ እየመጠኑ እንዲመገቡና እንዲጠጡ አደርጋለሁ። 17የእንጀራና የውሃ እጥረት ያጋጥማቸዋል፤ ስለዚህም ተስፋ በመቊረጥ እርስ በርሳቸው ይተያያሉ፤ ከበደላቸውም ብዛት የተነሣ ሰውነታቸው ይመነምናል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ