አስቴር 9:1-19
አስቴር 9:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን፣ በንጉሡ ትእዛዝ የወጣው ዐዋጅ የሚፈጸምበት ዕለት ነበር። በዚህም ዕለት የአይሁድ ጠላቶች የበላይነቱን እንደሚያገኙ ተማምነው ነበር፤ ሁኔታው ግን ተለወጠና አይሁድ በሚጠሏቸው ላይ የበላይነትን አገኙ። የእነርሱን መጥፋት በሚፈልጉ ወገኖች ላይ አደጋ ለመጣል አይሁድ በንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች ሁሉ ባሉት ከተሞቻቸው ተሰበሰቡ። የሌሎቹ አገር ዜጎች ሕዝብ ሁሉ ፈርተዋቸው ስለ ነበር፣ ማንም ሊደፍራቸው አልቻለም። የየአውራጃው መኳንንት ሁሉ፣ እንደራሴዎች፣ የአውራጃ ገዦች እንዲሁም የንጉሡ አስተዳዳሪዎች አይሁድን ረዷቸው፤ ይህን ያደረጉትም መርዶክዮስን ስለ ፈሩ ነበር። መርዶክዮስ በቤተ መንግሥቱ ታዋቂ ሆነ፤ ዝናው በየአውራጃው ሁሉ ተሰማ፤ ኀይሉም እየበረታ ሄደ። ስለዚህ አይሁድ ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሏቸው፤ አጠፏቸውም፤ በሚጠሏቸውም ላይ ደስ ያላቸውን አደረጉ። አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰው ገደሉ፤ አጠፉም። ፖርሻንዳታን፣ ደልፎንን፣ አስፓታን፣ ፖራታን፣ አዳልያን፣ አሪዳታን፣ ፓርማ ሽታን፣ አሪሳይን፣ አሪዳይንና ዋይዛታንም ገደሉ፤ እነዚህም የአይሁድ ጠላት የሆነው የሐመዳቱ ልጅ የሐማ ዐሥር ወንዶች ልጆች ነበሩ። በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም። በሱሳ ግንብ የተገደሉት ሰዎች ብዛት በዚያኑ ዕለት ለንጉሡ ተነገረው። ንጉሡም ንግሥት አስቴርን፣ “አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰውና ዐሥሩን የሐማ ልጆች ገድለዋል፤ አጥፍተዋልም። በተቀሩት በንጉሡ አውራጃዎችስ ምን አድርገው ይሆን? አሁንስ የምትለምኚው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ የምትጠይቂውስ ምንድን ነው? ይፈቀድልሻል” አላት። አስቴርም፣ “ንጉሥን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ የዛሬውን ዐዋጅ ነገም እንዲደግሙት ፈቃድህ ይሁን፤ ዐሥሩ የሐማ ወንዶች ልጆችም ዕንጨት ላይ ይሰቀሉ” አለች። ንጉሡም ይህ እንዲሆን አዘዘ። በሱሳ ዐዋጅ ተነገረ፤ ዐሥሩንም የሐማ ወንዶች ልጆች ሰቀሏቸው። በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ አዳር በተባለው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በአንድነት መጡ፤ በሱሳም ሦስት መቶ ሰዎች ገደሉ፤ በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም። በዚህ ጊዜ በሌሎች በንጉሡ አውራጃዎች የሚኖሩ የተቀሩት አይሁድ ራሳቸውን ለመከላከልና ከጠላቶቻቸውም ለመገላገል ተሰበሰቡ፤ ከሚጠሏቸውም ሰባ አምስት ሺሕ ገደሉ፤ በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም። ይህ የሆነው አዳር በተባለው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን ነበር፤ በዐሥራ አራተኛው ቀን ዐረፉ፤ ዕለቱንም የተድላና የደስታ ቀን አድርገው ዋሉ። በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ ግን በዐሥራ ሦስተኛውና በዐሥራ አራተኛው ቀን ተሰብስበው ነበር፤ ከዚያም በዐሥራ አምስተኛው ቀን ዐረፉ፤ ዕለቱንም የተድላና የደስታ ቀን አድርገው ዋሉ። በየመንደሩ የሚኖሩ የገጠር አይሁድ፣ የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛ ቀን የተድላና የደስታ፣ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚለዋወጡበት ቀን አድርገው የሚያከብሩት ከዚሁ የተነሣ ነው።
አስቴር 9:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አዳር በሚባለውም በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሦስተኛው ቀን፥ የንጉሡ ትእዛዝና አዋጅ ሊፈጸምበት በነበረው ቀን፥ የአይሁድ ጠላቶች ሊሠለጥኑባቸው በነበረው ቀን፥ አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ እንዲሠለጥኑ ነገሩ ተገለበጠ። አይሁድም ክፋታቸውን በሚሹት ሰዎች ላይ እጃቸውን ይዘረጉ ዘንድ በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በነበሩ ከተሞቻቸው ውስጥ ተሰበሰቡ፥ እነርሱንም መፍራት በአሕዛብ ሁሉ ላይ ወድቆ ነበርና እነርሱን የሚቃወም ሰው አልነበረም። መርዶክዮስን መፍራት በላያቸው ስለ ወደቀ በየአገሩ የነበሩ አዛውንትና ሹማምቶች አለቆችም፥ የንጉሡንም ሥራ የሚሠሩቱ ሁሉ አይሁድን አገዙ። ያ ሰው መርዶክዮስ ከፍ ከፍ እያለ ስለ ሄደ በንጉሡ ቤት ታላቅ ሆኖ ነበርና፥ የመርዶክዮስም ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰምቶ ነበርና። አይሁድም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሉአቸው፥ አጠፉአቸውም፥ በሚጠሉአቸውም ላይ እንደ ወደዱ አደረጉባቸው። አይሁድም በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ አጠፉም። ፈርሰኔስ፥ ደልፎን፥ ፋስጋ፥ ፋረዳታ፥ በርያ፥ ሰርባካ፥ መርመሲማ፥ ሩፋዮስ፥ አርሳዮስ፥ ዛቡታዮስ የሚባሉትን፥ የሐመዳቱን ልጅ የአይሁድን ጠላት አሥሩን የሐማን ልጆች ገደሉ፥ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። በዚያም ቀን በሱሳ ግንብ የተገደሉት ሰዎች ቍጥር ወደ ንጉሡ መጣ። ንጉሡም ንግሥቲቱን አስቴርን፦ አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰዎችንና አሥሩን የሐማ ልጆች ገደሉ አጠፉአቸውም፥ በቀሩትስ በንጉሡ አገሮች እንዴት አድርገው ይሆን! አሁንስ ልመናሽ ምንድር ነው? ይሰጥሻል፥ ሌላስ የምትሺው ምንድር ነው? ይደረጋል አላት። አስቴርም፦ ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ ዛሬ እንደ ተደረገው ትእዛዝ ነገ ደግሞ ያድርጉ፥ አሥሩም የሐማ ልጆች በግንድ ላይ ይሰቀሉ አለች። ንጉሡም ይህ ይደረግ ዘንድ አዘዘ፥ አዋጅም በሱሳ ተነገረ፥ አሥሩንም የሐማን ልጆች ሰቀሉ። በሱሳም የነበሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ደግሞ ተሰብስበው በሱሳ ሦስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ፥ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። የቀሩትም በንጉሡ አገር ያሉ አይሁድ ተሰብስበው ለሕይወታቸው ቆሙ፥ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ፥ ከሚጠሉአቸውም ሰባ አምስት ሺህ ገደሉ፥ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። አዳር በሚባለው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን ይህ ተደረገ፥ በአሥራ አራተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የግብዣና የደስታም ቀን አደረጉ። በሱሳ የነበሩት አይሁድ ግን በአሥራ ሦስተኛውና በአሥራ አራተኛው ቀን ተሰበሰቡ፥ በአሥራ አምስተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የመጠጥና የደስታም ቀን አደረጉት። ስለዚህም በመንደሮችና ባልተመሸጉ ከተሞች የሚኖሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውን ቀን የደስታና የመጠጥ የመልካምም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበት ቀን ያደርጉታል።
አስቴር 9:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን እነሆ ደረሰ፤ ያም ዕለት የአይሁድ ጠላቶች ሁሉ አይሁድን በቊጥጥራቸው ሥር ስለ ማድረግ የወጣውን ንጉሣዊ ዐዋጅ ለመፈጸም የተዘጋጁበት ቀን ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታው ተለውጦ አይሁድ በእነርሱ ላይ ድልን ተቀዳጁ። በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በየከተማው አይሁድ በመኖሪያ ሰፈራቸው ሁሉ ጒዳት ሊያደርስባቸው በሚፈልግ በማንኛውም ሰው ላይ አደጋ ለመጣል በሚያስችላቸው ሁኔታ ተደራጁ፤ በየትኛውም ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ስለ ፈሩአቸው ማንም እነርሱን ለመቋቋም አልደፈረም። እንዲያውም የየሀገሩ ገዢዎችና አስተዳዳሪዎች ሌሎችም ባለሥልጣኖችና የመንግሥት ተወካዮች ሁሉ አይሁድን ረዱአቸው፤ ይህንንም ያደረጉት መርዶክዮስን በመፍራት ነበር። መርዶክዮስ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥ በቤተ መንግሥት ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠው ታላቅ ሰው መሆኑና ኀይሉም እየበረታ መሄዱ በደንብ ታወቀ። በዚህ ዐይነት አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ የፈለጉትን ለማድረግ ቻሉ፤ በሰይፍ እያጠቁም ጨፈጨፉአቸው። አይሁድ መናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ብቻ እንኳ አምስት መቶ ሰው ፈጁ። ከነዚህም ውስጥ ፓርሻንዳታ፥ ዳልፎን፥ አስፓታ፥ ፖራታ፥ አዳልያ፥ አሪዳታ፥ ፓርማሽታ፥ አሪሳይ፥ አሪዳይና ዋይዛታ ተብለው የሚጠሩት የሃመዳታ ልጅ የሆነው የአይሁድ ጠላት የሃማን ልጆች ይገኙባቸዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን የንብረት ዝርፊያ አላካሄዱም። በዚያም ዕለት የተገደሉት ሰዎች ብዛት ምን ያኽል እንደ ሆነ ለንጉሡ ተነገረው። ንጉሡም ንግሥት አስቴርን “እነሆ አይሁድ መናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ብቻ እንኳ የገደሉአቸው ሰዎች ቊጥር ዐሥሩን የሃማንን ወንዶች ልጆች ጨምሮ አምስት መቶ ደርሶአል፤ በየሀገሩ የገደሉአቸውማ ከዚህ እጅግ ሳይበልጥ አይቀርም፤ ታዲያ፥ አሁን ከዚህ ሌላ ምን ትፈልጊያለሽ? ይፈጸምልሻል፤ የምትፈልጊውን ንገሪኝ ይሰጥሻል!” አላት። አስቴርም “የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ከሆነስ በሱሳ ከተማ የሚኖሩት አይሁድ ዛሬ ያደረጉትን በነገውም ዕለት ደግመው እንዲያደርጉት ይፈቀድላቸው፤ የዐሥሩም የሃማን ልጆች አስከሬን ተወሰዶ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል እዘዝ” ስትል መለሰችለት። ይህም እንዲፈጸም ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ በሱሳ ከተማም እንደገና ዐዋጅ ተነገረ፤ የሃማን ዐሥር ልጆች አስከሬንም በይፋ ለሕዝብ እንዲታይ ተደርጎ ተሰቀለ። አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ እንደገና በአንድነት ተደራጅተው በተጨማሪ ሦስት መቶ ሰዎችን ገደሉ፤ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ዘረፋ አላካሄዱም። እንዲሁም በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በየሀገሩ የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ አንድነታቸውን በማጠናከር ተደራጅተው ራሳቸውን ተከላከሉ፤ ይጠሉአቸው የነበሩትንም ሰባ አምስት ሺህ ሕዝብ በመግደል ከጠላቶቻቸው እጅ ራሳቸውን አዳኑ፤ ይሁን እንጂ ምንም ዐይነት የንብረት ዝርፊያ አላካሄዱም። ይህም የሆነው አዳር የተባለው ወር በገባ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ነበር፤ በተከታዩ ዐሥራ አራተኛ ቀን ግን ምንም ግድያ ሳያካሄዱ የተድላ ደስታ ቀን አድርገውት ዋሉ። በሱሳ ከተማ የሚኖሩት አይሁድ ግን በዐሥራ ሦስተኛውና በዐሥራ አራተኛው ቀን ሲገድሉ ቈይተው በዐሥራ አምስተኛው ቀን ስላቆሙ በዚሁ በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል አድርገው በተድላ ደስታ ዋሉ። በታናናሽ ከተሞች የሚኖሩ አይሁድ አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር ዐሥራ አራተኛውን ዕለት የበዓል ቀን በማድረግ ሲበሉና ሲጠጡ እርስ በርሳቸውም አንዱ ለሌላው የምግብ ስጦታ ሲለዋወጡ የሚውሉት ስለዚህ ነው።