የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 9:1-19

መጽሐፈ አስቴር 9:1-19 አማ05

አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን እነሆ ደረሰ፤ ያም ዕለት የአይሁድ ጠላቶች ሁሉ አይሁድን በቊጥጥራቸው ሥር ስለ ማድረግ የወጣውን ንጉሣዊ ዐዋጅ ለመፈጸም የተዘጋጁበት ቀን ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታው ተለውጦ አይሁድ በእነርሱ ላይ ድልን ተቀዳጁ። በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በየከተማው አይሁድ በመኖሪያ ሰፈራቸው ሁሉ ጒዳት ሊያደርስባቸው በሚፈልግ በማንኛውም ሰው ላይ አደጋ ለመጣል በሚያስችላቸው ሁኔታ ተደራጁ፤ በየትኛውም ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ስለ ፈሩአቸው ማንም እነርሱን ለመቋቋም አልደፈረም። እንዲያውም የየሀገሩ ገዢዎችና አስተዳዳሪዎች ሌሎችም ባለሥልጣኖችና የመንግሥት ተወካዮች ሁሉ አይሁድን ረዱአቸው፤ ይህንንም ያደረጉት መርዶክዮስን በመፍራት ነበር። መርዶክዮስ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት ውስጥ በቤተ መንግሥት ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠው ታላቅ ሰው መሆኑና ኀይሉም እየበረታ መሄዱ በደንብ ታወቀ። በዚህ ዐይነት አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ የፈለጉትን ለማድረግ ቻሉ፤ በሰይፍ እያጠቁም ጨፈጨፉአቸው። አይሁድ መናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ብቻ እንኳ አምስት መቶ ሰው ፈጁ። ከነዚህም ውስጥ ፓርሻንዳታ፥ ዳልፎን፥ አስፓታ፥ ፖራታ፥ አዳልያ፥ አሪዳታ፥ ፓርማሽታ፥ አሪሳይ፥ አሪዳይና ዋይዛታ ተብለው የሚጠሩት የሃመዳታ ልጅ የሆነው የአይሁድ ጠላት የሃማን ልጆች ይገኙባቸዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን የንብረት ዝርፊያ አላካሄዱም። በዚያም ዕለት የተገደሉት ሰዎች ብዛት ምን ያኽል እንደ ሆነ ለንጉሡ ተነገረው። ንጉሡም ንግሥት አስቴርን “እነሆ አይሁድ መናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ብቻ እንኳ የገደሉአቸው ሰዎች ቊጥር ዐሥሩን የሃማንን ወንዶች ልጆች ጨምሮ አምስት መቶ ደርሶአል፤ በየሀገሩ የገደሉአቸውማ ከዚህ እጅግ ሳይበልጥ አይቀርም፤ ታዲያ፥ አሁን ከዚህ ሌላ ምን ትፈልጊያለሽ? ይፈጸምልሻል፤ የምትፈልጊውን ንገሪኝ ይሰጥሻል!” አላት። አስቴርም “የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ከሆነስ በሱሳ ከተማ የሚኖሩት አይሁድ ዛሬ ያደረጉትን በነገውም ዕለት ደግመው እንዲያደርጉት ይፈቀድላቸው፤ የዐሥሩም የሃማን ልጆች አስከሬን ተወሰዶ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል እዘዝ” ስትል መለሰችለት። ይህም እንዲፈጸም ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ በሱሳ ከተማም እንደገና ዐዋጅ ተነገረ፤ የሃማን ዐሥር ልጆች አስከሬንም በይፋ ለሕዝብ እንዲታይ ተደርጎ ተሰቀለ። አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ እንደገና በአንድነት ተደራጅተው በተጨማሪ ሦስት መቶ ሰዎችን ገደሉ፤ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ዘረፋ አላካሄዱም። እንዲሁም በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በየሀገሩ የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ አንድነታቸውን በማጠናከር ተደራጅተው ራሳቸውን ተከላከሉ፤ ይጠሉአቸው የነበሩትንም ሰባ አምስት ሺህ ሕዝብ በመግደል ከጠላቶቻቸው እጅ ራሳቸውን አዳኑ፤ ይሁን እንጂ ምንም ዐይነት የንብረት ዝርፊያ አላካሄዱም። ይህም የሆነው አዳር የተባለው ወር በገባ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ነበር፤ በተከታዩ ዐሥራ አራተኛ ቀን ግን ምንም ግድያ ሳያካሄዱ የተድላ ደስታ ቀን አድርገውት ዋሉ። በሱሳ ከተማ የሚኖሩት አይሁድ ግን በዐሥራ ሦስተኛውና በዐሥራ አራተኛው ቀን ሲገድሉ ቈይተው በዐሥራ አምስተኛው ቀን ስላቆሙ በዚሁ በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል አድርገው በተድላ ደስታ ዋሉ። በታናናሽ ከተሞች የሚኖሩ አይሁድ አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር ዐሥራ አራተኛውን ዕለት የበዓል ቀን በማድረግ ሲበሉና ሲጠጡ እርስ በርሳቸውም አንዱ ለሌላው የምግብ ስጦታ ሲለዋወጡ የሚውሉት ስለዚህ ነው።