የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አስቴር 9

9
የአይሁድ ድል ማድረግ
1አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን፣ በንጉሡ ትእዛዝ የወጣው ዐዋጅ የሚፈጸምበት ዕለት ነበር። በዚህም ዕለት የአይሁድ ጠላቶች የበላይነቱን እንደሚያገኙ ተማምነው ነበር፤ ሁኔታው ግን ተለወጠና አይሁድ በሚጠሏቸው ላይ የበላይነትን አገኙ። 2የእነርሱን መጥፋት በሚፈልጉ ወገኖች ላይ አደጋ ለመጣል አይሁድ በንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች ሁሉ ባሉት ከተሞቻቸው ተሰበሰቡ። የሌሎቹ አገር ዜጎች ሕዝብ ሁሉ ፈርተዋቸው ስለ ነበር፣ ማንም ሊደፍራቸው አልቻለም። 3የየአውራጃው መኳንንት ሁሉ፣ እንደራሴዎች፣ የአውራጃ ገዦች እንዲሁም የንጉሡ አስተዳዳሪዎች አይሁድን ረዷቸው፤ ይህን ያደረጉትም መርዶክዮስን ስለ ፈሩ ነበር። 4መርዶክዮስ በቤተ መንግሥቱ ታዋቂ ሆነ፤ ዝናው በየአውራጃው ሁሉ ተሰማ፤ ኀይሉም እየበረታ ሄደ።
5ስለዚህ አይሁድ ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሏቸው፤ አጠፏቸውም፤ በሚጠሏቸውም ላይ ደስ ያላቸውን አደረጉ። 6አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰው ገደሉ፤ አጠፉም። 7ፖርሻንዳታን፣ ደልፎንን፣ አስፓታን፣ 8ፖራታን፣ አዳልያን፣ አሪዳታን፣ 9ፓርማ ሽታን፣ አሪሳይን፣ አሪዳይንና ዋይዛታንም ገደሉ፤ 10እነዚህም የአይሁድ ጠላት የሆነው የሐመዳቱ ልጅ የሐማ ዐሥር ወንዶች ልጆች ነበሩ። በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም።
11በሱሳ ግንብ የተገደሉት ሰዎች ብዛት በዚያኑ ዕለት ለንጉሡ ተነገረው። 12ንጉሡም ንግሥት አስቴርን፣ “አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰውና ዐሥሩን የሐማ ልጆች ገድለዋል፤ አጥፍተዋልም። በተቀሩት በንጉሡ አውራጃዎችስ ምን አድርገው ይሆን? አሁንስ የምትለምኚው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ የምትጠይቂውስ ምንድን ነው? ይፈቀድልሻል” አላት።
13አስቴርም፣ “ንጉሥን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ የዛሬውን ዐዋጅ ነገም እንዲደግሙት ፈቃድህ ይሁን፤ ዐሥሩ የሐማ ወንዶች ልጆችም ዕንጨት ላይ ይሰቀሉ” አለች።
14ንጉሡም ይህ እንዲሆን አዘዘ። በሱሳ ዐዋጅ ተነገረ፤ ዐሥሩንም የሐማ ወንዶች ልጆች ሰቀሏቸው። 15በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ አዳር በተባለው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በአንድነት መጡ፤ በሱሳም ሦስት መቶ ሰዎች ገደሉ፤ በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም።
16በዚህ ጊዜ በሌሎች በንጉሡ አውራጃዎች የሚኖሩ የተቀሩት አይሁድ ራሳቸውን ለመከላከልና ከጠላቶቻቸውም ለመገላገል ተሰበሰቡ፤ ከሚጠሏቸውም ሰባ አምስት ሺሕ ገደሉ፤ በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም። 17ይህ የሆነው አዳር በተባለው ወር ዐሥራ ሦስተኛ ቀን ነበር፤ በዐሥራ አራተኛው ቀን ዐረፉ፤ ዕለቱንም የተድላና የደስታ ቀን አድርገው ዋሉ።
የፉሪም በዓል መከበር
18በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ ግን በዐሥራ ሦስተኛውና በዐሥራ አራተኛው ቀን ተሰብስበው ነበር፤ ከዚያም በዐሥራ አምስተኛው ቀን ዐረፉ፤ ዕለቱንም የተድላና የደስታ ቀን አድርገው ዋሉ።
19በየመንደሩ የሚኖሩ የገጠር አይሁድ፣ የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛ ቀን የተድላና የደስታ፣ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚለዋወጡበት ቀን አድርገው የሚያከብሩት ከዚሁ የተነሣ ነው።
20መርዶክዮስ የተፈጸሙትን እነዚህን ድርጊቶች ጻፈ፤ ደብዳቤ አዘጋጅቶም በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃ በቅርብና በሩቅ ለሚገኙት አይሁድ ሁሉ ላከ፤ 21የላከውም የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ አምስተኛ ቀን በየዓመቱ እንዲያከብሩ ነው፤ 22የሚያከብሩበትም ምክንያት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍት ያገኙበት፣ ሐዘናቸው ወደ ደስታ፣ ልቅሷቸውም ወደ ክብረ በዓል የተለወጠበት ቀን ስለሆነ ነው። ቀኖቹንም የተድላና የደስታ ቀኖች አድርገው፣ እርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲያከብሩ ጻፈላቸው።
23ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ለመፈጸምና የጀመሩትን በዓል ለማክበር ተስማሙ፤ 24ምክንያቱም የአይሁድ ሁሉ ጠላት የሆነው የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፤ ሊፈጃቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የተባለ ዕጣ ጥሎ ነበር። 25ሤራው በንጉሡ ዘንድ እንደ ታወቀ#9፥25 ወይም፣ አስቴር በንጉሡ ፊት በወጣች ጊዜ ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ሤራ በገዛ ራሱ ላይ እንዲጠመጠም፣ እርሱና ወንዶች ልጆቹም በዕንጨት ላይ እንዲሰቀሉ የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ። 26ስለዚህ እነዚህ ቀኖች ፉር ከሚለው ቃል “ፉሪም” ለመባል በቁ። በዚህ ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ሁሉ፣ ስላዩትና ስለ ደረሰባቸውም ነገር ሁሉ፣ 27አይሁድ በታዘዘውና በተወሰነው ጊዜ እነርሱና ዘሮቻቸው፣ እነርሱን የተጠጓቸውም ሁሉ እነዚህን ሁለት ቀኖች በየዓመቱ ባለማቋረጥ እንዲያከብሩ ሥርዐት አድርገው ራሳቸው ወሰኑ። 28እነዚህም ቀኖች በእያንዳንዱ ትውልድ፣ በእያንዳንዱ ቤተ ሰብ፣ በእያንዳንዱ አውራጃና በእያንዳንዱ ከተማ መታሰብና መከበር ይኖርባቸዋል፤ ይኸውም እነዚህ የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ ሳይከበሩ እንዳይቀሩ፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል እንዳይደመሰስ ነው።
29ስለዚህ የአቢካኢል ልጅ ንግሥት አስቴር ከአይሁዳዊው ከመርዶክዮስ ጋር በመሆን፣ ፉሪምን አስመልክተው ይህችን ሁለተኛዪቱን ደብዳቤ ለማጽናት በሙሉ ሥልጣን ጻፉ። 30መርዶክዮስም የመልካም ምኞት መግለጫና ማረጋገጫ የሆነውን ደብዳቤ በጠረክሲስ ግዛት ውስጥ በሚገኙት አንድ መቶ ሃያ ሰባት አውራጃዎች ለሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ላከ፤ 31የላከውም አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ባወጁላቸውና እንደዚሁም የጾሙንና የሰቈቃውን ጊዜ በሚመለከት ለራሳቸውና ለዘራቸው ባጸኑት ውሳኔ መሠረት እነዚህ የፉሪም ቀኖች በተወሰነላቸው ጊዜ እንዲከበሩ ነው። 32የአስቴር ዐዋጅ ስለ ፉሪም የወጣውን ሥርዐት አጸና፤ ይህም በመዝገብ ተጻፈ።

Currently Selected:

አስቴር 9: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ