የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ አስቴር 9

9
1አዳር በሚባለውም በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሦስተኛው ቀን፥ የንጉሡ ትእዛዝና አዋጅ ሊፈጸምበት በነበረው ቀን፥ የአይሁድ ጠላቶች ሊሠለጥኑባቸው በነበረው ቀን፥ አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ እንዲሠለጥኑ ነገሩ ተገለበጠ። 2አይሁድም ክፋታቸውን በሚሹት ሰዎች ላይ እጃቸውን ይዘረጉ ዘንድ በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በነበሩ ከተሞቻቸው ውስጥ ተሰበሰቡ፥ እነርሱንም መፍራት በአሕዛብ ሁሉ ላይ ወድቆ ነበርና እነርሱን የሚቃወም ሰው አልነበረም። 3መርዶክዮስን መፍራት በላያቸው ስለ ወደቀ በየአገሩ የነበሩ አዛውንትና ሹማምቶች አለቆችም፥ የንጉሡንም ሥራ የሚሠሩቱ ሁሉ አይሁድን አገዙ። 4ያ ሰው መርዶክዮስ ከፍ ከፍ እያለ ስለ ሄደ በንጉሡ ቤት ታላቅ ሆኖ ነበርና፥ የመርዶክዮስም ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰምቶ ነበርና። 5አይሁድም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሉአቸው፥ አጠፉአቸውም፥ በሚጠሉአቸውም ላይ እንደ ወደዱ አደረጉባቸው። 6አይሁድም በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ አጠፉም። 7-8ፈርሰኔስ፥ ደልፎን፥ ፋስጋ፥ ፋረዳታ፥ 9በርያ፥ ሰርባካ፥ መርመሲማ፥ ሩፋዮስ፥ አርሳዮስ፥ 10ዛቡታዮስ የሚባሉትን፥ የሐመዳቱን ልጅ የአይሁድን ጠላት አሥሩን የሐማን ልጆች ገደሉ፥ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም።
11በዚያም ቀን በሱሳ ግንብ የተገደሉት ሰዎች ቍጥር ወደ ንጉሡ መጣ። 12ንጉሡም ንግሥቲቱን አስቴርን፦ አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰዎችንና አሥሩን የሐማ ልጆች ገደሉ አጠፉአቸውም፥ በቀሩትስ በንጉሡ አገሮች እንዴት አድርገው ይሆን! አሁንስ ልመናሽ ምንድር ነው? ይሰጥሻል፥ ሌላስ የምትሺው ምንድር ነው? ይደረጋል አላት። 13አስቴርም፦ ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ ዛሬ እንደ ተደረገው ትእዛዝ ነገ ደግሞ ያድርጉ፥ አሥሩም የሐማ ልጆች በግንድ ላይ ይሰቀሉ አለች። 14ንጉሡም ይህ ይደረግ ዘንድ አዘዘ፥ አዋጅም በሱሳ ተነገረ፥ አሥሩንም የሐማን ልጆች ሰቀሉ። 15በሱሳም የነበሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ደግሞ ተሰብስበው በሱሳ ሦስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ፥ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም።
16የቀሩትም በንጉሡ አገር ያሉ አይሁድ ተሰብስበው ለሕይወታቸው ቆሙ፥ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ፥ ከሚጠሉአቸውም ሰባ አምስት ሺህ ገደሉ፥ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። 17አዳር በሚባለው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን ይህ ተደረገ፥ በአሥራ አራተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የግብዣና የደስታም ቀን አደረጉ። 18በሱሳ የነበሩት አይሁድ ግን በአሥራ ሦስተኛውና በአሥራ አራተኛው ቀን ተሰበሰቡ፥ በአሥራ አምስተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የመጠጥና የደስታም ቀን አደረጉት። 19ስለዚህም በመንደሮችና ባልተመሸጉ ከተሞች የሚኖሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውን ቀን የደስታና የመጠጥ የመልካምም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበት ቀን ያደርጉታል።
20መርዶክዮስም ይህን ነገር ጻፈ፥ በንጉሡም በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በቅርብና በሩቅ ወዳሉት አይሁድ ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። 21በየዓመቱም አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውና አሥራ አምስተኛው ቀን፥ 22አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙበት ቀን፥ ወሩም ከኀዘን ወደ ደስታ ከልቅሶም ወደ መልካም ቀን የተለወጠበት ወር ሆኖ ይጠብቁት ዘንድ፥ የግብዣና የደስታም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበትና ለድሆች ስጦታ የሚሰጡበት ቀን ያደርጉት ዘንድ አዘዛቸው። 23አይሁድም ለመሥራት የጀመሩትን፥ መርዶክዮስም የጻፈላቸውን ያደርጉ ዘንድ ተቀበሉት፥ 24አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ የአይሁድ ሁሉ ጠላት ሐማ አይሁድን ያጠፋ ዘንድ ተተንኵሎ ነበር፥ ሊደመስሳቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የሚባል ዕጣ ጥሎ ነበር። 25አስቴርም ወደ ንጉሡ ፊት በገባች ጊዜ በአይሁድ ላይ የተተነኰለው ክፉ ተንኰል በራሱ ላይ እንዲመለስ፥ እርሱና ልጆቹም በግንድ ላይ እንዲሰቀሉ በደብዳቤው አዘዘ።
26ስለዚህም እነዚህ ቀኖች እንደ ፉርስም ፉሪም ተባሉ። በዚህም ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ቃል ሁሉ፥ ስላዩትና ስላገኙአቸውም ነገር ሁሉ፥ 27-28አይሁድ እነዚህን ሁሉ ቀኖች እንደ ጽሕፈቱና እንደ ጊዜው በየዓመቱ ይጠብቁ ዘንድ፥ እነዚህም ቀኖች በየትውልዳቸውና በየወገናቸው በየአገራቸውም በየከተማቸውም የታሰቡና የተከበሩ ይሆኑ ዘንድ፥ እነዚህም የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ እንዳይሻሩ፥ መታሰባቸውም ከዘራቸው እንዳይቈረጥ፥ በራሳቸውና በዘራቸው ወደ እነርሱም በተጠጉት ሁሉ ላይ እንዳይቀር ሥርዓት አድርገው ተቀበሉ።
29የአቢካኢልም ልጅ ንግሥቲቱ አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ይህችን ስለ ፉሪም የምትናገረውን ሁለተኛይቱን ደብዳቤ በሥልጣናቸው ሁሉ ያጸኑአት ዘንድ ጻፉ። 30ደብዳቤዎቹንም በአርጤክስስ መንግሥት በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ወዳሉ አይሁድ ሁሉ በሰላምና በእውነት ቃል ላኩ። 31እነዚህንም የፉሪም ቀኖች፥ አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥቲቱ አስቴር እንዳዘዙ፥ ለራሳቸውና ለዘራቸውም የጾማቸውንና የልቅሶአቸውን ነገር ለማክበር እንደ ተቀበሉ፥ በየጊዜያቸው ያጸኑ ዘንድ ጻፉ። 32የአስቴርም ትእዛዝ ይህን የፉሪምን ነገር አጸና፥ በመጽሐፍም ተጻፈ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ