ኤፌሶን 5:25-28
ኤፌሶን 5:25-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት፥ ራሱንም ስለ እርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደ ሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ። በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ፥ የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኵሰት እንዳያገኝባት፥ ቤተ ክርስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ፤ እንዲሁም ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው ይውደዱ፤ ሚስቱንም የወደደ ራሱን ወደደ።
ኤፌሶን 5:25-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በቃሉ አማካይነት በውሃ ዐጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ እንዲሁም ጕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና እንከን አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው። ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድድ ራሱን ይወድዳል።
ኤፌሶን 5:25-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤
ኤፌሶን 5:25-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ክርስቶስ ይህን ያደረገው ቤተ ክርስቲያንን ሊቀድሳት ፈልጎ ነው፤ የቀደሳትም በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ ነው። በዚህ ዐይነት ዕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም ይህን የመሰለ ሌላ መጥፎ ነገር ሳይገኝባት ቅድስት፥ እንከን የሌለባትና ውብ አድርጎ ወደራሱ ያቀርባታል። እንዲሁም ባሎች የገዛ ራሳቸውን እንደሚወዱ ሚስቶቻቸውን መውደድ ይገባቸዋል፤ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል።
ኤፌሶን 5:25-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ እንደሰጣት፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ከውሃ መታጠብ ጋር በቃሉ አንጽቶ እንዲቀድሳት፥ እንዲሁም ጉድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር የሌለባት አድርጎ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ ሊያቀርባ እንደፈለገ፥ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደገዛ አካላቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤