የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኤፌሶን 5

5
1እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤ 2ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ።
3ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኩሰት ወይም የሥሥት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና። 4የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰግኑ ሁኑ። 5ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ፣ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት#5፥5 ወይም የክርስቶስና የእግዚአብሔር መንግሥት በሆነው ርስት የለውም። 6ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው። 7ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ።
8ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ 9የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና። 10እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ። 11ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤ 12በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና። 13ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ 14ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣
“አንተ የተኛህ ንቃ፤
ከሙታን ተነሣ፤
ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሏል።
15እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። 16ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። 17ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ። 18በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና። 19በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። 20በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ።
21ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ።
ባልና ሚስት
5፥22–6፥9 ተጓ ምብ – ቈላ 3፥18–4፥1
22ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ 23ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። 24እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል።
25ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ 26በቃሉ አማካይነት በውሃ ዐጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ 27እንዲሁም ጕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው። 28ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድድ ራሱን ይወድዳል። 29የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው፤ 30እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና። 31“ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ”። 32ይህ ጥልቅ ምስጢር ነው፤ እኔም ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እናገራለሁ። 33ሆኖም ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር።

Currently Selected:

ኤፌሶን 5: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ