ኤፌሶን 3:14-19
ኤፌሶን 3:14-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህም በልቡናዬ ተንበርክኬ ለአብ እሰግዳለሁ። በሰማይና በምድር ያሉ ነገዶች ሁሉ ለሚጠሩት ለእርሱ፤ እንደ ጌትነቱ ምላት ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ያጸናችሁ ዘንድ። በልባችሁ ውስጥ በፍቅር ሥር መሠረታችሁ የጸና ሲሆን ክርስቶስ በሃይማኖት በሰው ውስጥ ያድራልና። ስፋቱና ርዝመቱ፥ ምጥቀቱና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ለማስተዋል ትችሉ ዘንድ፥ የክርስቶስን ፍቅር ለመረዳት፥ በእግዚአብሔር ፍጹምነት በሁሉ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ።
ኤፌሶን 3:14-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ ከእርሱም በሰማይና በምድር ያለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ ያገኛል። በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣ የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው። እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።
ኤፌሶን 3:14-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ።
ኤፌሶን 3:14-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ በእግዚአብሔር አብ ፊት በጒልበቴ ተንበርክኬ የምጸልየው በዚህ ምክንያት ነው። በሰማይና በምድር ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ እውነተኛ ስሙን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ውስጣዊውን ሰውነታችሁን የሚያጠነክር ኀይል በመንፈሱ አማካይነት ከክብሩ ባለጸግነት እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ። እንዲሁም ክርስቶስ በእምነት በልባችሁ እንዲኖርና እናንተም ሥር ሰዳችሁ በፍቅር የጸናችሁ እንድትሆኑ እጸልያለሁ። ደግሞም የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱና ርዝመቱ፥ ከፍታውና ጥልቀቱ፥ ምን ያኽል መሆኑን ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ማስተዋል እንድትችሉና ይህን ከሰው ዕውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር እንድታውቁ በእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ለመሞላትም እንድትበቁ እጸልያለሁ።
ኤፌሶን 3:14-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህም ምክንያት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ ከእርሱም በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ስያሜ ያገኛል። እንደ ክብሩ ባለጠግነት መጠን፥ በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ እጸልያለሁ፤ ሥር ሰዳችሁ፥ በፍቅርም ታንጻችሁ ክርስቶስ በልባችሁ በእምነት እንዲኖር፥ ስፋቱና ርዝመቱ፥ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ማስተዋል ላይ እንድትደርሱ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር፥ እጸልያለሁ፤ የእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ድረስ እንድትሞሉ፥ እውቀትን የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር እንድታውቁ ነው።