ኤፌሶን 3
3
ለአሕዛብ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ
1በዚህም ምክንያት እኔ ጳውሎስ ለእናንተ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ።
2ለእናንተ ጥቅም ሲባል ስለ ተሰጠኝ የእግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በርግጥ ሰምታችኋል፤ 3ቀደም ሲል በዐጭሩ እንደ ጻፍሁት፣ በመገለጥ እንዳውቀው የተደረገው ምስጢር ይህ ነው። 4እንግዲህ ይህን ስታነብቡ፣ የክርስቶስን ምስጢር እንዴት እንደማስተውል ለመረዳት ትችላላችሁ። 5ይህም ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያትና ነቢያት የተገለጠውን ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር። 6ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው።
7እኔም በኀይሉ አሠራር በተሰጠኝ በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኛለሁ። 8ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ። 9እንዲሁም ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት የተሰወረውን የዚህን ምስጢር አሠራር ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ። 10ሐሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው፤ 11ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በፈጸመው ዘላለማዊ ዕቅዱ መሠረት ነው። 12በእርሱና በእርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን። 13ስለዚህ ክብራችሁ በሆነው ስለ እናንተ በደረሰብኝ መከራ ተስፋ እንዳትቈርጡ ዐደራ እላችኋለሁ።
ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የተደረገ ጸሎት
14በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ 15ከእርሱም በሰማይና በምድር ያለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ#3፥15 ወይም አባትነት ሁሉ ያገኛል። 16በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ 17ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣ 18የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው። 19እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።
20እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ 21በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤ አሜን።
Currently Selected:
ኤፌሶን 3: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.