ኤፌሶን 3:1-13
ኤፌሶን 3:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህም ምክንያት እኔ ጳውሎስ ለእናንተ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ። ለእናንተ ጥቅም ሲባል ስለ ተሰጠኝ የእግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በርግጥ ሰምታችኋል፤ ቀደም ሲል በዐጭሩ እንደ ጻፍሁት፣ በመገለጥ እንዳውቀው የተደረገው ምስጢር ይህ ነው። እንግዲህ ይህን ስታነብቡ፣ የክርስቶስን ምስጢር እንዴት እንደማስተውል ለመረዳት ትችላላችሁ። ይህም ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያትና ነቢያት የተገለጠውን ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር። ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው። እኔም በኀይሉ አሠራር በተሰጠኝ በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኛለሁ። ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ። እንዲሁም ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት የተሰወረውን የዚህን ምስጢር አሠራር ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ። ሐሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው፤ ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በፈጸመው ዘላለማዊ ዕቅዱ መሠረት ነው። በእርሱና በእርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን። ስለዚህ ክብራችሁ በሆነው ስለ እናንተ በደረሰብኝ መከራ ተስፋ እንዳትቈርጡ ዐደራ እላችኋለሁ።
ኤፌሶን 3:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ አሕዛብ ሆይ ስለ እናንተ እኔ ጳውሎስ የክርስቶስ እስረኛው ነኝ። ስለ እናንተ የሰጠኝን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ስጦታ ሰምታችኋል። አስቀድሞ በጥቂቱ እንደ ጻፍሁላችሁ ይህን ምሥጢር ገልጦ አሳይቶኛልና። ይህንም በምታነቡበት ጊዜ፥ የክርስቶስን ምሥጢር ማስተዋሌን ለማወቅ ትችላላችሁ። በሌላ ዘመን ለሰው ልጆች ያልተገለጠ ዛሬ ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ለነቢያቱ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተገለጠ፥ አሕዛብን ወራሾቹና አካሉ ያደርጋቸው ዘንድ፥ በወንጌልም ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ተስፋ አንድ ይሆኑ ዘንድ። በኀይሉ አጋዥነት እንደ ሰጠኝ እንደ ጸጋው ስጦታ መጠን እኔ መልእክተኛና አዋጅ ነጋሪ የሆንሁለት፥ ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ አስተምር ዘንድ ይህን ጸጋ ሰጠኝ። ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ከዘለዓለም የተሰወረ የዚህ ምሥጢር ሥርዐትንም ለሁሉ እገልጥ ዘንድ፤ ብዙ ልዩ ልዩ የሆነች የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ ዓለም ሳይፈጠር የወሰናት፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም የፈጸማት፥ እኛ ጸጋንና ባለሟልነትን ያገኘንበት፥ በሃይማኖት ወደሚገኘው ተስፋም ያደረሰበት፤ ስለዚህም ስለ እናንተ ለክብራችሁ የምታገኘኝን መከራዬን ቸል እንዳይላት እግዚአብሔርን እማልደዋለሁ።
ኤፌሶን 3:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህም አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ የክርስቶስ ኢየሱስ እስር የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እንበረከካለሁ። ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም። እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠንየወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት። ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ፤ ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥ በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን። ስለዚህ ስለ እናንተ ስላለ መከራዬ እንዳትታክቱ እለምናችኋለሁ፥ ክብራችሁ ነውና።
ኤፌሶን 3:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ እኔ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንኩት ለእናንተ ለአሕዛብ ስል ነው። ለእናንተ ጥቅም እንዳውለው እግዚአብሔር በጸጋው የአገልግሎት ዕድል እንደ ሰጠኝ በእርግጥ ሰምታችኋል። አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍኩላችሁ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ገልጦ በራእይ አሳይቶኛል። ይህን የጻፍኩላችሁንም ስታነቡ ስለ ክርስቶስ ምሥጢር እኔ ያስተዋልኩትን ለመረዳት ትችላላችሁ። ይህም ምሥጢር በእግዚአብሔር መንፈስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ነቢያቱ አሁን እንደተገለጠው ዐይነት ባለፉት ዘመናት ለነበሩት ሰዎች አልተገለጠም። ይህም የሚያመለክተው አሕዛብ ከአይሁድ ጋር የርስቱ ወራሾችና የአንድ አካል ክፍሎች ሆነው እግዚአብሔር ለሰጠው ተስፋ በወንጌል አማካይነት በኢየሱስ ክርስቶስ ተካፋዮች መሆናቸውን ነው። እግዚአብሔር በኀይሉ አሠራር በሰጠኝ የጸጋ ስጦታ እኔም የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኜአለሁ። እኔ ከቅዱሳን ሁሉ የማንስ ብሆንም እንኳ ወሰን የሌለውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ እንዳበሥር በእግዚአብሔር ጸጋ ይህ ዕድል ተሰጠኝ። እንዲሁም ባለፉት ዘመናት ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ተሰውሮ ስለ ነበረው ምሥጢር የእግዚአብሔር ዕቅድ ምን እንደ ሆነ ለሁሉ እንድገልጥ ጸጋ ተሰጠኝ። ይህም የሆነው በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት በሰማይ ያሉት አለቆችና ባለሥልጣኖች የእግዚአብሔርን ጥበብ በየመልኩ እንዲያውቁ ነው። እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የፈጸመው በዘለዓለማዊው ዕቅዱ መሠረት ነው። የክርስቶስ በመሆናችንና በእርሱ በማመናችን በእግዚአብሔር ፊት በድፍረትና በመተማመን መቅረብ እንችላለን። እኔ ስለ እናንተ የምቀበለው መከራ ክብራችሁ ነው፤ ስለዚህ በመከራዬ ምክንያት ተስፋ አትቊረጡ ብዬ እለምናችኋለሁ።
ኤፌሶን 3:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ ነው እኔ ጳውሎስ ለክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆንኩት። በእርግጥ ስለ እናንተ ሲባል ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ ይህ ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋሪያትና ለነቢያት በመንፈስ እንደተገለጠው ባለፉት ትውልዶች ለነበሩ አልተገለጠም ነበር። ይህ የሆነው፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም አማካኝነት በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነውን የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ ነው። ለዚህ ወንጌል በኀይሉ አሠራር እንደተሰጠኝ እንደ የእግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን አገልጋይ ሆንኩ። ከቅዱሳን ሁሉ ያነስኩ ብሆንም፥ ወሰን የሌለውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እንድሰብክ፥ ይህ ጸጋ ለኔ ተሰጠ፤ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘለዓለም የተሰወረው የምሥጢር አሳብ ምን እንደሆነ ለሁሉ እንድገልጥ፥ በዚህም ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት እንድትታወቅ ነው። ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘለዓለም አሳብ ነበረ። በእርሱም ባለን እምነት አማካኝነት በድፍረትና በመተማመን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን። ስለዚህ፥ ክብራችሁ ነውና፥ ስለ እናንተ ስለምቀበለው መከራዬ እንዳትታክቱ እለምናችኋለሁ።