መክብብ 4:13-16
መክብብ 4:13-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ድሃና ጠቢብ ብላቴና ከእንግዲህ ወዲህ ተግሣጽን መቀበል ከማያውቅ ከሰነፍ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል። በመንግሥቱ ችግረኛ ቢሆንም ከግዞት ቤት ለመንገሥ ወጥቶአልና። ከፀሓይ በታች የሚሄዱትን ሕያዋን ሁሉ በእርሱ ፋንታ ከሚነሣው ከሌላው ጐልማሳ ጋር ሆነው አየሁ። ከእርሱ በፊት የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ቍጥር የላቸውም፤ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህ ደግሞ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
መክብብ 4:13-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ምክርን መቀበል ከማያውቅ ሞኝና ሽማግሌ ንጉሥ ይልቅ ጠቢብ የሆነ ድኻ ወጣት ይሻላል። ወጣቱ ከእስር ቤት ወደ ንጉሥነት የመጣ ወይም በግዛቱ ውስጥ በድኽነት የተወለደ ሊሆን ይችላል። ከፀሓይ በታች የሚኖሩና የሚመላለሱ ሁሉ፣ ንጉሡን የሚተካውን ወጣት ተከትለውት አየሁ። በፊቱ የነበረው ሕዝብ ሁሉ ቍጥር ስፍር አልነበረውም፤ ከርሱ በኋላ የመጡት ግን በተተኪው አልተደሰቱም። ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
መክብብ 4:13-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ድሀና ጠቢብ ብላቴና ተግሣጽን መቀበል ከእንግዲህ ወዲህ ከማያውቅ ከሰነፍ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል። ምንም በመንግሥቱ አገር ደግሞ ችግረኛ ሆኖ ቢወለድ፥ ከግዞቱ ቤት ወደ መንግሥት ወጥቶአልና። ከፀሐይ በታች የሚሄዱትን ሕያዋን ሁሉ በእርሱ ፋንታ ከሚነሣው ከሌላው ጎበዝ ጋር ሆነው አየሁ። ከእርሱ በፊት የተገዙለት ሕዝብ ሁሉ አይቈጠሩም፥ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
መክብብ 4:13-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ምክርን ከማይቀበል ከሞኝ ሽማግሌ ንጉሥ ብልኅ ድኻ ወጣት ይሻላል። ምንም እንኳ አንድ ሰው ከድኻ ቢወለድና እስረኛ የነበረ ቢሆንም ንጉሥ ለመሆን ይችላል። አንድ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ሁሉ በንጉሡ ቦታ የሚተካውን ወጣት ሲከተሉ አየሁ። ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድርበት ጊዜ የሚገዛለት ሕዝብ ብዛት እጅግ ብዙ ነው፤ ከዙፋኑ ላይ በታጣ ጊዜ ግን ስላደረገው ነገር ሁሉ የሚያመሰግነው አንድ ሰው እንኳ አይገኝለትም፤ ይህም ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር የሚቈጠር ከንቱ ነገር ነው።
መክብብ 4:13-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ድኀና ጠቢብ ወጣት ተግሣጽን መቀበል ካቃተው አላዋቂ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል። ምንም እንኳን ችግረኛ ሆኖ ቢወለድ፥ ከእስር ቤት ለመንገሥ ወጥቶአልና። ከፀሐይ በታች የሚሄዱት ሕያዋን በሙሉ እርሱን የተካውን ወጣት ሲከተሉ አየሁ። ከእርሱ በፊት የተገዙለት ሕዝብ ሁሉ ስፍር ቍጥር አልነበራቸውም፥ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህም ደግሞ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።