መክብብ 10:1-9
መክብብ 10:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ በስንፍናም ካለ ታላቅ ክብር ይልቅ ትንሽ ጥበብ ትበልጣለች። የጠቢብ ልብ በስተቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተግራው ነው። ደግሞም ሰነፍ በልቡ ፈቃድና መንገድ በሚሄድ ጊዜ አእምሮ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ሰንፍና ነው። ትዕግሥት ታላቁን ኀጢአት ያስተሰርያልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ ባለማወቅ የሚወጣ ስሕተት ነው፥ ሰነፍ በታላቅ ማዕርግ ላይ ተሾመ፥ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። አገልጋዮች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ፥ መኳንንትም እንደ አገልጋዮች በምድር ላይ በእግራቸው ሲሄዱ አየሁ። ለባልንጀራው ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ ዕንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል።
መክብብ 10:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሞቱ ዝንቦች ሽቱን እንደሚያገሙ፣ ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ያቀልላል። የጠቢብ ልብ ወደ ቀኝ፣ የሞኝ ልብ ግን ወደ ግራ ያዘነብላል። ሞኝ በጐዳና ሲሄድ ልበ ቢስ ነው፤ ጅል መሆኑንም ለማንም ይገልጻል። የገዥ ቍጣ በተነሣብህ ጊዜ፣ ስፍራህን አትልቀቅ፤ ትዕግሥት ታላቁን ጥፋት ጸጥ ያደርጋልና። ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፤ ይህም ከገዥ የሚወጣ ስሕተት ነው፤ ሞኞች በብዙ የክብር ስፍራዎች ሲቀመጡ፣ ሀብታሞች ግን በዝቅተኛ ስፍራ ሆነዋል። መሳፍንት እንደ ባሮች በእግራቸው ሲሄዱ፣ ባሮች ፈረስ ላይ ተቀምጠው አይቻለሁ። ጕድጓድን የሚምስ ራሱ ይገባበታል፤ ቅጥርንም የሚያፈርስ እባብ ይነድፈዋል። ድንጋይ የሚፈነቅል ይጐዳበታል፤ ግንድንም የሚፈልጥ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።
መክብብ 10:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፥ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል። የጠቢብ ልብ በስተ ቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተ ግራው ነው። ደግሞም ሰነፍ በመንገድ ሲመላለስ እርሱ ልብ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ስንፍና ነው። ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፥ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ፥ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። ባሪያዎች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ መሳፍንትም እንደ ባሪያዎች በምድር ላይ ሲሄዱ አየሁ። ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ እንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል።
መክብብ 10:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሞቱ ዝንቦች ተቀምሞ የተሠራውን የዘይት ሽቶ ሊያገሙት ይችላሉ፤ እንዲሁም ትንሽ ሞኝነት ታላቅ ጥበብን ያጠፋል። ጥበበኛ መልካም ነገር መሥራቱ፥ ሞኝም መሳሳቱ የተለመደ ተግባር ነው። ሞኝ ሰው በሚተላለፍበት መንገድ ሁሉ ያለ ሐሳብ ይራመዳል፤ ለሰውም ሁሉ ሞኝነቱን ያሳውቃል። ጸጥ ብለህ ብትታገሥ ከባድ ለሆነው በደልህ እንኳ ይቅርታ ማግኘት ስለምትችል አለቃህ በተቈጣህ ጊዜ የሥራ ቦታህን አትልቀቅ፤ በዓለም ላይ ሌላም ክፋት አይቻለሁ፤ ይኸውም ገዢዎች የሚፈጽሙት ግፍ ነው። ሞኞች ከፍተኛ ሥልጣን ሲያገኙ ባለጸጎች ግን ችላ ተብለው ዝቅተኛ ስፍራ ይዘዋል። መሳፍንት እንደ አገልጋዮች በእግራቸው ሲሄዱ፥ አገልጋዮች ግን በፈረስ ተቀምጠው ሲጓዙ አየሁ። ጒድጓድን የሚቈፍር ሰው ራሱ ይወድቅበታል፤ ቅጽርንም የሚያፈርስ በእባብ ይነደፋል፤ ድንጋይን የሚፈነቅል በፈነቀለው ድንጋይ ራሱ ይጐዳል፤ እንጨትን የሚፈልጥ በፈለጠው እንጨት ይቈስላል።
መክብብ 10:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፥ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል። የጠቢብ ልብ በስተ ቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተ ግራው ነው። ደግሞም ሰነፍ በመንገድ ሲመላለስ እርሱ ልብ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ስንፍና ነው። ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቁጣ የተነሣብህ እንደሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፥ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ፥ ባለ ጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። ባርያዎች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ መሳፍንትም እንደ ባርያዎች በምድር ላይ ሲሄዱ አየሁ። ጉድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ እንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል።