የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 10

10
1የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፥ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል። 2የጠቢብ ልብ በስተ ቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተ ግራው ነው። 3ደግሞም ሰነፍ በመንገድ ሲመላለስ እርሱ ልብ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ስንፍና ነው።
4ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። 5ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፥ 6ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ፥ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። 7ባሪያዎች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ መሳፍንትም እንደ ባሪያዎች በምድር ላይ ሲሄዱ አየሁ።
8ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። 9ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ እንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል። 10ብረት ቢደነዝዝ ሰውም ባይስለው ኃይልን ሊያበዛ ይገባዋል፥ ጥበብ ግን ሥራውን ለማከናወን ትጠቅመዋለች። 11ደጋሚ ሳይደግምባት እባብ ብትነድፍ ለደጋሚው ትርፍ የለውም።
12የጠቢብ ሰው የአፉ ቃል ሞገስ ናት፥ የሰነፍ ከንፈሮች ግን ራሱን ይውጡታል። 13የአፉ ቃል መጀመሪያ ስንፍና ነው፥ የንግግሩ ፍጻሜም ክፉ እብደት ነው። 14ሰነፍ ቃሉን ያበዛል፥ ሰው ግን የሚሆነውን አያውቅም፥ ከእርሱስ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል? 15የሰነፍ ሥራ ያደክመዋል ወደ ከተማ መሄድ አያውቅምና።
16ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ ወዮልሽ! 17ንጉሥሽ የከበረ ልጅ የሆነ፥ ለብርታት እንጂ ለስካር ያይደለ በጊዜ የሚበሉ መኳንንት ያሉሽ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ የተመሰገንሽ ነሽ። 18ተግባር በመፍታት ጣራው ይዘብጣል፥ በእጅም መታከት ቤት ያፈስሳል። 19እንጀራን ለሳቅ የወይን ጠጅንም ለሕይወት ደስታ ያደርጉታል፥ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል። 20የሰማይ ወፍ ቃሉን ይወስደዋልና፥ ባለ ክንፎችም ነገሩን ይናገራሉና በልብህ አሳብ እንኳ ቢሆን ንጉሥን አትስደብ፥ በመኝታ ቤትህም ባለጠጋን አትስደብ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ