የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 9

9
1ጻድቃንና ጠቢባን ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፥ ፍቅር ወይም ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም ሁሉ ወደ ፊታቸው ነው። 2የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፥ እንደ መልካሙ ሰው እንዲሁ ኃጢአተኛው፥ እንደ መሐለኛው ሰው እንዲሁ መሐላን የሚፈራው ነው። 3አንድ ድርሻ ሁሉን እንዲያገኝ ከፀሐይ በታች በተደረገው ሁሉ ይህ ነገር ክፉ ነው፥ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ነው፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። 4ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። 5ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፥ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፥ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። 6ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።
7እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። 8ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፥ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። 9በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። 10አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።
11እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፥ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። 12ሰውም ጊዜውን አያውቅም፥ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ።
13ከፀሐይ በታችም ይህን ጥበብ አየሁ፥ እርስዋም በእኔ ዘንድ ታላቅ መሰለችኝ። 14ታናሽ ከተማ ነበረች፥ ጥቂቶች ሰዎችም ነበሩባት፥ ታላቅ ንጉሥም መጣባት ከበባትም፥ ታላቅ ግንብም ሠራባት። 15ጠቢብ ድሀ ሰውም ተገኘባት፥ ያችንም ከተማ በጥበቡ አዳናት፥ ያን ድሀ ሰው ግን ማንም አላሰበውም። 16እኔም፦ ከኃይል ይልቅ ጥበብ ትበልጣለች፥ የድሀው ጥበብ ግን ተናቀች ቃሉም አልተሰማችም አልሁ።
17በሰነፎች መካከል ከሚጮኽ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች። 18ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፥ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ