የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አሞጽ 7:1-17

አሞጽ 7:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ አሳ​የኝ፤ እነ​ሆም ከም​ሥ​ራቅ አን​በጣ ይመ​ጣል፤ አን​ዱም ኵብ​ኵባ ንጉሡ ጎግ ነበረ። የም​ድ​ሩ​ንም ሣር በልቶ ይጨ​ር​ሳል፤ እኔም፥ “ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሆይ! ይቅር እን​ድ​ትል እለ​ም​ን​ሃ​ለሁ፤ ያዕ​ቆ​ብን ማን ያነ​ሣ​ዋል? ጥቂት ነውና” አልሁ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ስለ​ዚህ ነገር ራራ፤ “ይህ አይ​ሆ​ንም፤” ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እን​ዲህ አሳ​የኝ፤ እነ​ሆም ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለመ​ፍ​ረድ በቃሉ እሳ​ትን ጠራ፤ እር​ስ​ዋም ታላ​ቁን ቀላ​ይና ምድ​ርን በላች። እኔም፥ “ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሆይ! እን​ድ​ት​ተው እለ​ም​ን​ሃ​ለሁ፤ ያዕ​ቆ​ብን ማን ያነ​ሣ​ዋል? ጥቂት ነውና” አልሁ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ስለ​ዚህ ነገር ራራ፤ “ይህ ደግሞ አይ​ሆ​ንም፥” ይላል ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ አሳ​የኝ፤ እነ​ሆም አንድ ሰው በቱ​ንቢ በተ​ሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር፤ በእ​ጁም ቱንቢ ነበር። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም፥ “አሞጽ ሆይ! የም​ታ​የው ምን​ድን ነው?” አለኝ። እኔም፥ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም፥ “እነሆ! በሕ​ዝቤ በእ​ስ​ራ​ኤል መካ​ከል ቱንቢ አደ​ር​ጋ​ለሁ፤ ከእ​ን​ግ​ዲ​ህም ወዲህ ደግሞ ይቅር አል​ላ​ቸ​ውም። መሳ​ቂያ የሆኑ የኮ​ረ​ብ​ታው መስ​ገ​ጃ​ዎች ይፈ​ር​ሳሉ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም መቅ​ደ​ሶች ባድማ ይሆ​ናሉ፤ በኢ​ዮ​ር​ብ​ዓ​ምም ቤት ላይ በሰ​ይፍ እነ​ሣ​ለሁ” አለ። የቤ​ቴ​ልም ካህን አሜ​ስ​ያስ ወደ እስ​ራ​ኤል ንጉሥ ወደ ኢዮ​ር​ብ​ዓም ልኮ፥ “አሞጽ በእ​ስ​ራ​ኤል ቤት መካ​ከል ዐም​ፆ​ብ​ሃል፤ ምድ​ሪ​ቱም ቃሉን ሁሉ ልት​ሸ​ከም አት​ች​ልም” አለ። አሞጽ፥ “ኢዮ​ር​ብ​ዓም በሰ​ይፍ ይሞ​ታል፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ከሀ​ገሩ ተማ​ርኮ ይሄ​ዳል” ብሎ​አ​ልና። አሜ​ስ​ያ​ስም አሞ​ጽን፥ “ባለ ራእዩ ሆይ! ሂድ፤ ወደ ይሁዳ ምድር ሽሽ፤ በዚ​ያም ተቀ​መጥ፥ በዚ​ያም ትን​ቢ​ትን ተና​ገር፤ ነገር ግን ቤቴል የን​ጉሥ መቅ​ደ​ስና የመ​ን​ግ​ሥት ቤት ናትና ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትን​ቢት አት​ና​ገር” አለው። አሞ​ጽም መልሶ አሜ​ስ​ያ​ስን አለው፥ “እኔ ላም ጠባ​ቂና በለስ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነ​ቢይ ልጅ አይ​ደ​ለ​ሁም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በጎ​ቹን ከመ​ከ​ተል ወሰ​ደኝ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም፦ ሂድ፥ ለሕ​ዝቤ ለእ​ስ​ራ​ኤል ትን​ቢት ተና​ገር አለኝ። አሁ​ንም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል ስማ፤ አንተ፦ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ትን​ቢት አት​ና​ገር፥ የያ​ዕ​ቆ​ብ​ንም ቤት አት​ዘ​ብ​ዝ​ባ​ቸው ብለ​ሃል። ስለ​ዚህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦ ሚስ​ትህ በከ​ተ​ማ​ይቱ ውስጥ አመ​ን​ዝራ ትሆ​ና​ለች፤ ወን​ዶ​ችና ሴቶች ልጆ​ች​ህም በሰ​ይፍ ይወ​ድ​ቃሉ፤ ምድ​ር​ህም በገ​መድ ትከ​ፈ​ላ​ለች፤ አን​ተም በረ​ከ​ሰች ምድር ትሞ​ታ​ለህ፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ከም​ድሩ ተማ​ርኮ ይሄ​ዳል።”

አሞጽ 7:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጌታ እግዚአብሔር ይህን አሳየኝ፤ የንጉሡ የመኸር እህል ከተሰበሰበ በኋላ ገቦው መብቀል በጀመረ ጊዜ፣ እርሱ የአንበጣ መንጋ እንዲፈለፈል አደረገ። አንበጦች የምድሩን ሣር ግጠው ከጨረሱት በኋላ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ!” አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ። እግዚአብሔርም “ይህ አይፈጸምም” አለ። ጌታ እግዚአብሔር ይህንም አሳየኝ፤ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ሊፈርድ ተዘጋጀ፤ እሳቱም ታላቁን ጥልቅ አደረቀ፤ ምድሪቱንም በላ። ከዚያም በኋላ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንድትተወው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ!” አልሁ። እግዚአብሔር ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ጌታ እግዚአብሔር፣ “ይህም ደግሞ አይፈጸምም” አለ። ይህንም ደግሞ አሳየኝ፤ ጌታ በእጁ ቱንቢ ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር አጠገብ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔር፣ “አሞጽ፣ የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም፣ “ቱንቢ” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ አልምራቸውም። “የይሥሐቅ ማምለኪያ ኰረብቶች ባድማ ይሆናሉ፤ የእስራኤል መቅደሶች ይፈርሳሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፌ እነሣለሁ።” ከዚህ በኋላ የቤቴል ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል በአንተ ላይ እያሤረ ነው፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም፤ አሞጽ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበርና፤ “ ‘ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፤ እስራኤልም በርግጥ ከትውልድ አገሩ ተማርኮ ይሄዳል።’ ” አሜስያስም፣ አሞጽን እንዲህ አለው፤ “አንተ ባለራእይ ከዚህ ሂድ! ከይሁዳ ምድር ሽሽ፤ እዚያም እንጀራህን ብላ፤ በዚያም ትንቢት ተናገር። ከእንግዲህ ወዲያ ግን በቤቴል ትንቢት አትናገር፤ የንጉሡ መቅደስ፣ የመንግሥቱም መኖሪያ ነውና።” አሞጽም ለአሜስያስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ እረኛና የባሉጥ ፍሬ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ እግዚአብሔር ግን የበግ መንጋ ከምጠብቅበት ቦታ ወስዶ፣ ‘ሂድና ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር’ አለኝ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። “አንተ፣ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፤ በይሥሐቅም ቤት ላይ አትስበክ’ ትላለህ። “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ሚስትህ በከተማዪቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ምድርህም በገመድ እየተለካ ይከፋፈላል፤ አንተ ራስህ በረከሰ ምድር ትሞታለህ፤ እስራኤልም ከትውልድ አገሩ፣ ተማርኮ ይሄዳል።’ ”

አሞጽ 7:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፥ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ። የምድሩንም ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፥ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድትተው እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም፦ አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም፦ እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፥ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፥ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ። የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ልኮ፦ አሞጽ፦ ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል ብሎአልና አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል ዐምፆብሃል፥ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም አለ። አሜስያስም አሞጽን፦ ባለ ራእዩ ሆይ፥ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ በዚያም ትንቢትን ተናገር፥ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር አለው። አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው፦ እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፥ እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ። አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፥ አንተ፦ በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል፥ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፥ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።

አሞጽ 7:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጌታ እግዚአብሔር ይህን ራእይ አሳየኝ፤ እነሆ የንጉሡ የመከር እህል ከታጨደ በኋላ እንደገና ገቦ ሆኖ በበቀለው እህል ላይ እግዚአብሔር የአንበጣ መንጋ እንዲፈለፈል አደረገ፤ አንበጦቹም የምድሩን ልምላሜ ሁሉ ግጠው እንደ በሉት ባየሁ ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ የሕዝብህን በደል ይቅር በል! ሕዝብህ እስራኤል ዐቅም ስለሌላቸው እንዴት ተቋቊመው መኖር ይችላሉ?” እግዚአብሔርም ራርቶላቸው “ይህ ያየኸው ነገር አይፈጸምም!” አለኝ። ጌታ እግዚአብሔር የገለጠልኝ ሌላውም ራእይ ይህ ነው፤ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር የእሳት ቅጣት ፍርድ አስተላለፈ፤ እሳቱም ባሕሩን በልቶ ካደረቀው በኋላ ምድርን ማቃጠል ጀመረ። በዚያን ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ እሳቱ እንዲቆም አድርግ! ሕዝብህ እስራኤል ዐቅም የሌላቸው ስለ ሆኑ እንዴት ተቋቊመው መኖር ይችላሉ?” እግዚአብሔርም ራርቶላቸው “ይህም ደግሞ አይፈጸምም” አለኝ። እግዚአብሔር ሌላ ራእይ ገለጠልኝ፤ እነሆ እግዚአብሔር በቱምቢ ተስተካክሎ በተሠራ ቅጽር አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ በእጁም ቱምቢ ይዞ ነበር፤ እርሱም “አሞጽ ሆይ! የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም “ቱምቢ ነው” አልኩ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “በቱምቢ ተስተካክሎ እንዳልተሠራ ቅጽር ሕዝቤ እስራኤል ጠማሞች ሆነው ስለ ተገኙ ይህ ቱምቢ የእስራኤልን ጠማማነት ማሳያ ምሳሌ ነው፤ ሳልቀጣቸውም አላልፍም። የይስሐቅና የልጅ ልጆቹ ከፍተኛ የመስገጃ ቦታዎች ይፈራርሳሉ፤ የእስራኤልም የተቀደሱ ቦታዎች ፈራርሰው ወና ይሆናሉ፤ የኢዮርብዓምን መንግሥት ፈጽሞ አጠፋለሁ።” የቤትኤል ካህን የሆነው አሜስያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ላከ፦ “እነሆ አሞጽ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሆኖ በአንተ ላይ እያሤረብህ ነው፤ ሕዝቡ የእርሱን ንግግር ሊታገሥ አይችልም። እርሱም ‘ኢዮርብዓም በጦርነት ይሞታል፤ የእስራኤልም ሕዝብ ከሀገራቸው ተማርከው ይሄዳሉ’ ይላል።” አሜስያስ አሞጽን እንዲህ አለው፦ “አንተ ባለ ራእይ! ወደ ይሁዳ ተመልሰህ ሂድና በዚያ ትንቢት እየተናገርክ መተዳደሪያህን አግኝ። ቤትኤል ግን የንጉሡ መስገጃና የሕዝቡም ቤተ መቅደስ ስለ ሆነች በዚህች ቦታ ዳግመኛ ትንቢት እንዳትናገር።” አሞጽም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ እኮ የመንጋዎች እረኛና የሾላ ፍሬ ተንከባካቢ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ ነገር ግን የበግ መንጋ ከምጠብቅበት ቦታ ወስዶ ‘ሂድ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር’ ብሎ ያዘዘኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው። አሁንም እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ስማ፤ አንተ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፤ የይስሐቅ ዘሮች የሆኑትንም የእስራኤልን ሕዝብ አትስበክ’ ብለህ ከልክለኸኛል። ስለዚህም አሜስያስ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፦ ‘ሚስትህ በከተማይቱ አመንዝራ ትሆናለች፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በጦርነት ይሞታሉ፤ ርስትህንም ባዕዳን በገመድ ለክተው ይከፋፈሉታል፤ አንተም በአሕዛብ ምድር ትሞታለህ፤ የእስራኤልም ሕዝብ ያለ ጥርጥር ተማርከው ከአገራቸው ይወሰዳሉ።’ ”

አሞጽ 7:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ መከር ካለፈ በኋላ ያለው እህል በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለ ነበረ። የምድሩንም እጽዋት በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ አይሆንም፥” ይላል ጌታ። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርሷም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ ደግሞ አይሆንም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። ጌታም፦ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ዳግመኛ አላልፋቸውም፤ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ።” የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም እንዲህ ብሎ ላከ፦ “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል አሢሮብሃል፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም። አሞጽ፦ ‘ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል’ ብሎ ተናግሮዋልና።” አሜስያስም አሞጽን እንዲህ አለው፦ “ባለ ራእዩ ሆይ! ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ዳግመኛ ትንቢት አትናገር።” አሞጽም ለአሜስያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ እኔ የመንጋዎች ጠባቂና የወርካ ዛፎችን ተንከባካቢ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ ጌታም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ ጌታም፦ “ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር” አለኝ። “አሁን ደግሞ የጌታን ቃል ስማ፤ አንተ፦ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ’ አልህ፤ ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ እየተለካች ትከፋፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።’ ”