ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ መከር ካለፈ በኋላ ያለው እህል በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለ ነበረ። የምድሩንም እጽዋት በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ አይሆንም፥” ይላል ጌታ። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርሷም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ ደግሞ አይሆንም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። ጌታም፦ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ዳግመኛ አላልፋቸውም፤ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ።” የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም እንዲህ ብሎ ላከ፦ “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል አሢሮብሃል፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም። አሞጽ፦ ‘ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል’ ብሎ ተናግሮዋልና።” አሜስያስም አሞጽን እንዲህ አለው፦ “ባለ ራእዩ ሆይ! ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ዳግመኛ ትንቢት አትናገር።” አሞጽም ለአሜስያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ እኔ የመንጋዎች ጠባቂና የወርካ ዛፎችን ተንከባካቢ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ ጌታም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ ጌታም፦ “ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር” አለኝ። “አሁን ደግሞ የጌታን ቃል ስማ፤ አንተ፦ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ’ አልህ፤ ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ እየተለካች ትከፋፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።’ ”
ትንቢተ አሞጽ 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 7:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች