የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ አሞጽ 7:1-17

ትንቢተ አሞጽ 7:1-17 አማ54

ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፥ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ። የምድሩንም ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፥ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድትተው እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም፦ አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም፦ እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፥ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፥ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ። የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ልኮ፦ አሞጽ፦ ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል ብሎአልና አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል ዐምፆብሃል፥ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም አለ። አሜስያስም አሞጽን፦ ባለ ራእዩ ሆይ፥ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ በዚያም ትንቢትን ተናገር፥ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር አለው። አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው፦ እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፥ እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ። አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፥ አንተ፦ በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል፥ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፥ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።