የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ አሞጽ 7

7
ጌታ ለነቢዩ አሞጽ ያሣየው ራእይ
1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ መከር ካለፈ በኋላ ያለው#7፥1 የሚሆነው። እህል በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለ ነበረ። 2የምድሩንም እጽዋት በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። 3ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ አይሆንም፥” ይላል ጌታ።
4ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርሷም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። 5እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። 6ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ ደግሞ አይሆንም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። 8ጌታም፦ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ዳግመኛ አላልፋቸውም፤ 9የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ።”
አሜስያስ ነቢዩ አሞጽን መቃወሙ
10የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም እንዲህ ብሎ ላከ፦ “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል አሢሮብሃል፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም። 11አሞጽ፦ ‘ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል’ ብሎ ተናግሮዋልና።” 12አሜስያስም አሞጽን እንዲህ አለው፦ “ባለ ራእዩ ሆይ! ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ 13ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ዳግመኛ ትንቢት አትናገር።”
14አሞጽም ለአሜስያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ እኔ የመንጋዎች ጠባቂና የወርካ#7፥14 ሾላ። ዛፎችን ተንከባካቢ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ 15ጌታም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ ጌታም፦ “ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር” አለኝ። 16“አሁን ደግሞ የጌታን ቃል ስማ፤ አንተ፦ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ’ አልህ፤ 17ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ እየተለካች ትከፋፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ያለ ጥርጥር ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።’ ”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ