ትንቢተ አሞጽ 6

6
እስራኤል በራስ መተማመንዋና ትዕቢትዋ ማብቃቱ
1በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተማምነው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው! 2ወደ ካልኔ እለፉና ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን? 3ክፉውን ቀን ከእናንተ ታርቃላችሁን? የግፍንስ ወንበር ታቀርባላችሁን? 4ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥ 5በበገናም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም ለራሳችሁ የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥ 6በፋጋ#6፥6 በቀድሞ ዘመን ከትልቅ ቅል ተሰብሮ፥ ተቀፎና መሀል ለመሐል ተቀዶ፥ የተከረከመ፥ ለተለያዩ ፈሳሽ ነገሮች መጠጫነት የሚያገለግል ነው። የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ቅባትም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ!
7ስለዚህ በመጀመሪያ ተማርከው ከሚፈልሱት ይሆናሉ፥ እንደ ፈቃዳቸው ከሚሆኑ መካከል ፈንጠዝያ ይርቃል። 8ጌታ እግዚአብሔር፦ “የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ የንጉሥ ቅጥሮቹንም ጠልቻለሁ፤ ስለዚህ ከተማይቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ” ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ። 9እንዲህም ይሆናል፤ ዐሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ። 10የሞተውን ሰው የሚያቃጥለው ዘመዱ አጥንቱን ከቤቱ አንስቶት ባወጣው ጊዜ፥ በቤቱም በውስጠኛው ክፍል ያለውን፦ “በእዚያ እስከ አሁን ድረስ ከአንተ ጋር ሰው አለን?” ይለዋል፥ እርሱም፦ “ማንም የለም” ይላል፤ ያንጊዜ፦ “የጌታን ስም ልንጠራ አይገባንምና ዝም በል” ይለዋል። 11እነሆም፥ ጌታ ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። 12በውኑ ፈረሶች በዓለታም መሬት ላይ ይጋልባሉን? ወይስ ሰው በበሬዎች በዚያ ላይ ሊያርስ ይችላልን? ነገር ግን እናንተ ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት ለወጣችሁ፤ 13በሎዴባር ደስ የሚላችሁ፥ እናንተም፦ “በብርታታችን ቃርናይምን ለራሳችን አልወሰድንምን?” የምትሉ ናችሁ። 14“የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ፥ እኔ አሕዛብን አስነሣባችኋለሁ፥” ይላል ጌታ የሠራዊት አምላክ፤ “እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ