2 ሳሙኤል 22:21-33

2 ሳሙኤል 22:21-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ጽድቄ ይከ​ፍ​ለ​ኛል፤ እንደ እጄ ንጽ​ሕ​ናም ይመ​ል​ስ​ል​ኛል፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ገድ ጠብ​ቄ​አ​ለ​ሁና፥ በአ​ም​ላ​ኬም አላ​መ​ፅ​ሁ​ምና። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበ​ርና፤ ጽድ​ቁም ከእኔ አል​ራ​ቀ​ምና። በእ​ርሱ ዘንድ ንጹሕ እሆ​ና​ለሁ፤ ከዐ​መ​ፃ​ዬም ራሴን እጠ​ብ​ቃ​ለሁ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽ​ሕና በዐ​ይ​ኖቹ ፊት መለ​ሰ​ልኝ። ከጻ​ድቅ ጋር ጻድቅ ትሆ​ና​ለህ፤ ከን​ጹሕ ሰውም ጋር ንጹሕ ትሆ​ና​ለህ፤ ከተ​መ​ረ​ጠም ጋር የተ​መ​ረጠ ትሆ​ና​ለህ፤ ከጠ​ማማ ጋርም ጠማማ ትሆ​ና​ለህ። አንተ የተ​ዋ​ረ​ደ​ውን ሕዝብ ታድ​ና​ለ​ህና፤ የት​ዕ​ቢ​ተ​ኞ​ችን ዐይ​ኖች ግን ታዋ​ር​ዳ​ለህ። አቤቱ! አንተ መብ​ራቴ ነህና፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ጨለ​ማ​ዬን ያበ​ራ​ል​ኛ​ልና። በአ​ንተ ብቻ​ዬን እሮ​ጣ​ለ​ሁና፤ በአ​ም​ላ​ኬም ቅጥ​ሩን እዘ​ል​ላ​ለ​ሁና። የኀ​ያል አም​ላክ መን​ገድ ንጹሕ ነው፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ጽኑዕ ነው፤ በእ​ሳ​ትም የጋለ ነው፤ በእ​ር​ሱም ለሚ​ታ​መ​ኑት ጠባ​ቂ​ያ​ቸው ነው። ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በቀር ጽኑዕ ማን ነው? ከአ​ም​ላ​ካ​ች​ንስ በቀር ፈጣሪ ማን ነው? በኀ​ይል የሚ​ያ​ጸ​ናኝ ኀያል እርሱ ነው፤ መን​ገ​ዴ​ንም ንጹሕ አድ​ርጎ አዘ​ጋጀ፤

2 ሳሙኤል 22:21-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም። ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም። በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤ ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፣ በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ። “ለታማኝ ሰው ታማኝ መሆንህን፣ ለፍጹም ሰው ፍጹም መሆንህን ታሳያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣ ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ። አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤ ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፣ ትዕቢተኞችን ይመለከታል። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ጕልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ። “የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው፤ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ማን አምላክ አለ? ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው? ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣ መንገዴንም የሚያቀና እርሱ አምላኬ ነው።

2 ሳሙኤል 22:21-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፥ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል፥ የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁምና። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ከሥርዓቱም አልራቅሁምና። በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ። ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፥ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፥ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ። አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና፥ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ኃይል በጭፍራ ላይ እሮጣለሁና፥ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና። የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥

2 ሳሙኤል 22:21-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕናም ይመልስልኛል። እኔ የእግዚአብሔርን መንገድ ተከትያለሁ፤ ፊቴን ከአምላኬ በመመለስ ክፉ ነገር አላደረግሁም። የእግዚአብሔርን ሕጎች ሁሉ እፈጽማለሁ፤ ሥርዓቱንም ከማክበር ወደ ኋላ አላልኩም። በእርሱ ዘንድ ንጹሕ ነበርኩ፥ ከኃጢአትም ራሴን ጠብቄአለሁ፤ እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና ዋጋዬን ከፈለኝ። አምላክ ሆይ! ለአንተ ታማኞች ለሆኑት ታማኝ ነህ፤ እውነተኞች ለሆኑትም እውነተኛ ነህ። ለንጹሖች ንጹሕ ነህ፤ ለጠማሞች ግን ተገቢ ዋጋቸውን ትሰጣለህ። ትሑቶችን ታድናለህ፤ ትዕቢተኞችን ግን ታዋርዳለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ለእኔ ብርሃኔ ነህ፤ አንተ አምላኬ ጨለማዬን ታበራለህ። በአንተ ርዳታ አንድ የጦር ጓድ አጠቃለሁ፤ አንተ አምላኬም ቅጥሩን ለመዝለል ትረዳኛለህ። የእግዚአብሔር መንገድ ፍጹም ነው፤ ቃሉ የጠራ ነው፤ እርሱን መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ማን ነው አምላክ? ከእርሱስ በቀር መጠጊያ የሚሆን ማነው? ብርታትን የሚሰጠኝና መንገዴን የሚያቃናልኝ እግዚአብሔር ነው።

2 ሳሙኤል 22:21-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታ እንደጽድቄ መለሰልኝ፤ እንደ እጄም ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ፤ የጌታን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ ከአምላኬ ክፋት በማድረግ አልተለየሁም። ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁም። በፊቱ ያለ ነውር ነበርሁ፤ ራሴንም ከኃጢአት ጠብቄአለሁ። ጌታም እንደጽድቄ፥ በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራትን ከፈለኝ። “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ፥ ለቅን ሰው አንተም ቅን ሆነህ ትታያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ ሆነህ ትታያለህ፥ ለጠማማ ሰው ግን ጠማማ ሆነህ ትታያለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህ፤ ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፥ ትዕቢተኞችን ይመለከታል። ጌታ ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ ጌታም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ርዳታ ሠራዊት አልፌ ወደ ፊት እሮጣለሁ፤ በአምላኬም ኃይል ቅጥሩን እዘላለሁ። የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የጌታም ቃል የጠራ ነው፤ ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤ ከጌታ በቀር አምላክ ማን ነው፤ ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቀና እግዚአብሔር ነው።