2 ሳሙኤል 14:1-33
2 ሳሙኤል 14:1-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሶርህያ ልጅ ኢዮአብም የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ ዐወቀ። ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና፥ “አልቅሺ፤ የኀዘንም ልብስ ልበሺ፤ ዘይትም አትቀቢ፤ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅስ ሴት ሁኚ፤ ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው” አላት፤ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ። እንዲሁም የቴቁሔዪቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግንባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፤ ሰግዳም “ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ፤ አድነኝ” አለች። ንጉሡም፥ “ምን ሆነሻል?” አላት። እርስዋም አለች፥ “በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ። ለእኔም ለአገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ በሜዳም ተጣሉ፤ የሚገላግላቸውም አልነበረም፤ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው። እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሡ፤ ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፤ እንዲሁም ደግሞ ለባሌ ስምና ዘር በምድር ላይ እንዳይቀር ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፤” ንጉሡም ሴቲቱን፥ “ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ” አላት። የቴቁሔዪቱም ሴት ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኀጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን” አለችው። ንጉሡም፥ “የሚናገርሽ ማን ነው? አምጪልኝ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም” አለ። ያችም ሴት፥ “ለመግደል ባለ ደሞች እንዳይበዙ፤ ልጄንም እንዳይገድሉብኝ ንጉሥ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ያስብ” አለች። እርሱም፥ “የልጅሽስ አንዲት የራሱ ጠጕር በምድር ላይ እንዳትወድቅ ሕያው እግዚአብሔርን” አላት። ሴቲቱም፥ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር” አለች፤ እርሱም፥ “ተናገሪ” አላት። ሴቲቱም አለች፥ “በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለምን አሰብህ? ወይስ ንጉሥ ያሳደደውን ስላላስመለሰ እንደ በደል ከንጉሥ አፍ ይህ ቃል ወጥቶአልን? ሞትን እንሞታለንና፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ እንሆናለንና፥ እግዚአብሔርም ነፍስን ይወስዳል። የተጣለውንም ከእርሱ ያርቅ ዘንድ ያስባል። አሁንም ሕዝቡ ስለሚያዩኝ ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፤ እኔም አገልጋይህ፦ የእኔን የአገልጋዩን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደ ሆነ ለጌታዬ ለንጉሥ ልናገር፤ እኔንና ልጄን ከእግዚአብሔር ርስት ያርቀን ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ አገልጋዩን ይሰማል አልሁ።” ያችም ሴት አለች፥ “መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ መሥዋዕትና እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል እንደዚሁ ነው፤ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን።” ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ፥ “የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ” አላት። ሴቲቱም፥ “ጌታዬ ንጉሥ ይናገር” አለች። ንጉሡም፥ “በዚህ ሁሉ ነገር የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር አለን?” አላት። ሴቲቱም ንጉሡን አለችው፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፤ አገልጋይህ ኢዮአብ አዝዞኛል፤ ይህንም ቃል ሁሉ በአገልጋይህ አፍ አደረገው። ይህን ነገር እናገር ዘንድ እንድመጣ ይህን ምክር ያደረገ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። ጌታዬ ግን በዚህ ዓለም የሚደረገውን ሁሉ ታውቅ ዘንድ እንደ መልአከ እግዚአብሔር ጥበብ ጥበበኛ ነህ፤” ንጉሡም ኢዮአብን፥ “እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፤ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው” አለው። ኢዮአብም በምድር ላይ በግንባሩ ወድቆ ሰገደለት፤ ንጉሡንም አመሰገነ፤ ኢዮአብም፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የአገልጋይህን ነገር አድርገሃልና በዐይንህ ፊት ሞገስን እንዳገኘ አገልጋይህ ዛሬ ዐወቀ” አለ። ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌድሶር ሄደ፤ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። ንጉሡም፥ “ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ” አለ፤ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም። በእስራኤል ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ ያማረ ሰው አልነበረም፤ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም። ቀድሞ በመጀመሪያ ዘመን ጠጕሩ ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቈረጠው ነበር፤ ሲቈረጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዝን ነበር። ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት። የሴቲቱ ልጅም ስም ትዕማር ይባላል። ያችውም ሴት መልከ መልካም ነበረች፤ እርሷም የሰሎሞን ልጅ የሮብአም ሚስት ሆና አቢያን ወለደችለት። አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም። አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፤ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፤ ሁለተኛም ላከበት፤ ሊመጣ ግን አልወደደም። አቤሴሎምም ብላቴኖቹን፥ “በእርሻዬ አጠገብ ያለችውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፤ በዚያም ገብስ አለው፤ ሄዳችሁ በእሳት አቃጥሉት” አላቸው። የአቤሴሎምም ብላቴኖች እርሻውን አቃጠሉት። የኢዮአብም አሽከሮች ልብሶቻቸውን ቀድደው ተመልሰው፥ “የአቤሴሎም አሽከሮች እርሻህን በእሳት አቃጠሉት” ብለው ነገሩት። ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና፥ “ብላቴኖችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት?” አለው። አቤሴሎምም ኢዮአብን፥ “ከጌድሶር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጬ ቢሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሥ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ና ብዬ ወደ አንተ ላክሁ፤ አሁንም የንጉሡን ፊት አላየሁም፤ ኀጢአት ቢኖርብኝ ይግደለኝ” አለው። ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፤ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ ሰገደለት፤ በንጉሡም ፊት ወደ ምድር በግንባሩ ወደቀ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።
2 ሳሙኤል 14:1-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ ተረዳ። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ቴቁሔ፤ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ሐዘንተኛ በመምሰል የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት መስለሽም ታዪ። ከዚያም ወደ ንጉሡ ሄደሽ እንዲህ በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ የምትናገራቸውን ቃላት ነገራት። የቴቁሔዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፣ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት በግምባሯ ተደፍታ እጅ በመንሣት አክብሮቷን ከገለጠች በኋላ፣ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች። ንጉሡም፣ “ችግርሽ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃት። እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤ እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፣ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው። እነሆ ቤተ ዘመዱ ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፣ ‘ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለንና ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፣ ከዚያም ወራሽ አልባ ትሆኛለሽ’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።” ንጉሡም ሴቲቱን፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ስለ ጕዳይሽ አስፈላጊውን ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት። ነገር ግን የቴቁሔዪቱም ሴት፣ “ንጉሥ ጌታዬ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች። ንጉሡም፣ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አያስቸግርሽም” ሲል መለሰላት። እርሷም፣ “ደም ተበቃዮቹ ልጄን በማጥፋት የባሰ ጕዳት እንዳያደርሱ፣ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ይለምን” አለች። ንጉሡም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ጠጕር እንኳ አትነካም” አላት። ከዚያም ሴቲቱ፣ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፣ “ዕሺ ተናገሪ” አላት። ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለችው፣ “እንዲህ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ንጉሡ ከአገር የተሰደደውን ልጁን አልመለሰውም፤ ታዲያ ይህን ሲናገር በራሱ ላይ መፍረዱ አይደለምን? በመሬት ላይ የፈሰሰ ውሃ እንደማይታፈስ ሁሉ፣ እኛም እንደዚሁ እንሞታለን፤ እግዚአብሔር ግን ከአገር የተሰደደ ሰው ከርሱ እንደ ራቀ በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም። “አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ይህን አሰብሁ፤ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊነቅለን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’ “አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆነ፣ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ እግዚአብሔር አምላክህም ካንተው ጋራ ይሁን’ ትላለች።” ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፣ “እኔም ለምጠይቅሽ ነገር አንቺም መልሱን አትደብቂኝ” አላት። ሴቲቱም፣ “ንጉሥ ጌታዬ፤ ዕሺ ይናገር” አለችው። ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት። ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። አዎን ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አንደበት እንዲነገር የላከኝ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ የመሰለ ጥበብ ስላለው፣ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።” ንጉሡም ኢዮአብን፣ “መልካም ነው፤ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው። ኢዮአብም አክብሮቱን ለንጉሡ ለመግለጥ ወደ መሬት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባረከ፣ ኢዮአብም በመቀጠል፣ “ንጉሡ የአገልጋዩን ልመና ስለ ተቀበለው፣ ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቱን ዛሬ ለማወቅ ችሏል” አለ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ጌሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው። ንጉሡ ግን፣ “እዚያው እቤቱ ይሂድ፤ ዐይኔን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም። መቼም በመልኩ ማማር አቤሴሎምን የሚያህል አንድም ሰው በመላው እስራኤል አልነበረም፤ ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚወጣለት እንከን አልነበረም። የራስ ጠጕሩ ሲከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ የተቈረጠውን በሚመዝነው ጊዜ ክብደቱ በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ይሆን ነበር። አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የተባለች አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ ሴት ልጁም በጣም ውብ ነበረች። አቤሴሎም የንጉሡን ዐይን ሳያይ ሁለት ዓመት በኢየሩሳሌም ኖረ። ከዚያም አቤሴሎም ወደ ንጉሡ እንዲሄድለት ኢዮአብን አስጠራው፤ ኢዮአብ ግን ወደ እርሱ መምጣት አልፈለገም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ላከበት፤ ኢዮአብ አሁንም መምጣት አልፈለገም። ከዚያም አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ “ተመልከቱ የኢዮአብ ዕርሻ የሚገኘው ከእኔ ዕርሻ አጠገብ ነው፤ በዕርሻው ላይ የገብስ አዝመራ አለው፤ ሄዳችሁም እሳት ልቀቁበት” አላቸው። ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች ሄደው የኢዮአብን ዕርሻ በእሳት አቃጠሉት። ከዚያም ኢዮአብ ወደ አቤሴሎም ቤት ሄደ፣ “አገልጋዮችህ ለምንድን ነው ዕርሻዬን ያቃጠሉት?” ብሎ ጠየቀው። አቤሴሎምም፣ ኢዮአብን፣ “ከጌሹር ለምን መጣሁ? ‘ለእኔ እስካሁንም እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር ብሏል ብለህ እንድትነግርልኝ ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ና’ ብዬ አስጠራሁህ፤ አሁንም ቢሆን፤ የንጉሡን ዐይን ማየት እፈልጋለሁ፤ ምንም ዐይነት በደል ከተገኘብኝ ይግደለኝ” አለው። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ ይህንኑ ነገረው። ከዚያም ንጉሡ አቤሴሎምን አስጠራው፤ እርሱም መጥቶ በንጉሡ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።
2 ሳሙኤል 14:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ አወቀ። ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና፦ አልቅሺ፥ የኅዘንም ልብስ ልበሺ፥ ዘይትም አትቀቢ፥ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅሺ ሁኚ፥ ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው አላት፥ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ። እንዲሁም የቴቁሔይቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግምባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፥ እጅ ነሥታም፦ ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ አለች። ንጉሡም፦ ምን ሆነሻል? አላት። እርስዋም መልሳ አለች፦ ክ በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ። ለእኔም ለባሪያህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፥ በሜዳም ተጣሉ፥ የሚገላግላቸውም አልነበረም፥ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው። እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፦ ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፥ እንዲሁም ደግሞ ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፥ የባሌን ስምና ዘርም ከምድር ላይ አያስቀሩም። ንጉሡም ሴቲቱን፦ ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ አላት። የቴቁሔይቱም ሴት ንጉሡን፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኃጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፥ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን አለችው። ንጉሡም፦ የሚናገርሽን አምጪልኝ፥ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም አለ። እርስዋም፦ ደም ተበቃዮችም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይጠፉ ልጄንም እንዳይገድሉ፥ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ያስብ አለች። እርሱም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ አንድ ጠጕር በምድር ላይ አይወድቅም አለ። ሴቲቱም፦ እኔ ባሪያህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር አለች፥ እርሱም፦ ተናገሪ አለ። ሴቲቱም አለች፦ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለምን አሰብህ? ንጉሡ ይህን ነገር ተናግሮአልና ያሳደደውን ስላላስመለሰ በደለኛ ነው። ሁላችን እንሞታለን፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ ነን፥ እግዚአብሔርም የነፍስን ጥፋት አይወድድም፥ ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ በምክሩ ያስባል። አሁንም ሕዝቡ ስለሚያስፈራኝ ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፥ እኔም ባሪያህ፦ ምናልባት የእኔን የባሪያውን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደሆነ ለንጉሡ ልናገር፥ እርስዋንና ልጅዋን ከእግዚአብሔር ርስት ያጠፋቸው ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ ባሪያውን ይሰማል አልሁ። እኔም ባሪያህ፦ መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኛል፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን አልሁ። ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ፦ የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ አላት። ሴቲቱም፦ ጌታዬ ንጉሥ ይናገር አለች። ንጉሡም፦ በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር ነውን? አላት። ሴቲቱም መልሳ፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝ ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፥ ባሪያህ ኢዮአብ አዝዞኛል፥ ይህንም ቃል ሁሉ በባሪያህ አፍ አደረገው። ባሪያህ ኢዮአብ የዚህ ነገር መልክ እንዲለውጥ አደረገ፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ጠቢብ እንደ ሆነ፥ አንተም ጌታዬ በምድር ላይ ያለውን ነገር ሁሉ ታውቅ ዘንድ ጠቢብ ነህ አለች። ንጉሡም ኢዮአብን፦ እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፥ እንግዲህ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው አለው። ኢዮአብም በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ እጅ ነሣ፥ ንጉሡንም ባረከ፥ ኢዮአብም፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የባሪያህን ነገር አድርገሃልና በዓይንህ ፊት ሞገስ እንዳገኘ ባሪያህ ዛሬ አወቀ አለ። ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፥ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ መጣ። ንጉሡም፦ ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ አለ፥ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ሄደ፥ የንጉሡንም ፊት አላየም። በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም፥ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም። ጠጕሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቆርጠው ነበር፥ ሲቆርጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር። ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፥ የሴቲቱም ልጅ ስም ትዕማር ነበረ፥ እርስዋም የተዋበች ሴት ነበረች። አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ። አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፥ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፥ ሁለተኛም ላከበት፥ ሊመጣ ግን አልወደደም። ባሪያዎቹንም፦ በእርሻዬ አጠገብ ያለውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፥ በዚያም ገብስ አለው፥ ሂዳችሁ በእሳት አቃጥሉት አላቸው። የአቤሴሎምም ባሪያዎች እርሻውን አቃጠሉት። ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና፦ ባሪያዎችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት? አለው። አቤሴሎምም ኢዮአብን መልሶ፦ ከጌሹር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጩ ብሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ጠራሁህ፥ አሁንም የንጉሡን ፊት ልይ፥ ኃጢአት ቢሆንብኝ ይግደለኝ አለው። ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፥ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ በንጉሥ ፊት ወደ ምድር በግምባሩ ተደፋ፥ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።
2 ሳሙኤል 14:1-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሡ ዳዊት አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ፤ ስለዚህም በተቆዓ የምትኖረውን አንዲት ብልኅ ሴት አስጠራ፤ እርስዋም በደረሰች ጊዜ “ሐዘንተኛ ለመምሰል ሞክሪ፤ የሐዘን ልብስሽን ልበሺ፤ ቅቤም አትቀቢ፤ ለብዙ ጊዜ በሐዘን ላይ የቈየሽ ሴት ለመምሰል ተዘጋጂ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ንጉሡ ቀርበሽ እኔ የምነግርሽን ንገሪው” አላት፤ ከዚህ በኋላ እርስዋ ልትናገረው የሚገባትን ሁሉ ኢዮአብ ነገራት። ሴቲቱም ወደ ንጉሡ ቀርባ ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሣችና “ንጉሥ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው። ንጉሡም “ምን ችግር አጋጠመሽ?” አላት፤ እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “እኔ ባሌ የሞተብኝ መበለት ሴት ነኝ፤ ንጉሥ ሆይ! እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ አንድ ቀን ገላጋይ በሌለበት ስፍራ ሁለቱ ልጆቼ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ አንዱ ሌላውን ገደለው፤ ንጉሥ ሆይ! እነሆ አሁን ዘመዶቼ ሁሉ በእኔ በአገልጋይህ ላይ ተነሥተው ‘ወንድሙን ስለ ገደለ ወራሽ እንኳ ብናጠፋ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን ሰው ስጪን’ እያሉ አስቸገሩኝ። ታዲያ፥ እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ የቀረኝን አንድ ተስፋ ሊያጠፉብኝና በምድርም ላይ የባሌን ስምና ዘር ሊያሳጡ ነው።” ንጉሡም “ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ ጉዳይ አዛለሁ” አላት። እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! አንተ ስለምታደርገው ነገር ሁሉ እኔና ቤተሰቤ እንወቀስበት አንተና ዙፋንህ ግን ንጹሓን ሁኑ” አለችው። ንጉሡም “ማንም ሰው ማንኛውንም ችግር ቢያመጣብሽ ወደ እኔ አምጪው ዳግመኛ ሊያስቸግርሽም አይችልም” አላት። እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! የልጄን ሞት ለመበቀል ኀላፊነት የተቀበለው ዘመዴ ሌላውን ልጄን በመግደል የባሰ ወንጀል እንዳይፈጽም ታደርገው ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ” አለችው። ንጉሥ ዳዊትም “በልጅሽ ላይ ጒዳት መድረስ ይቅርና ከራስ ጠጒሩ እንኳ አንዲቱ መሬት ላይ እንደማትወድቅ በሕያው እግዚአብሔር ስም ቃል እገባልሻለሁ” አላት። ሴቲቱም “ንጉሥ ሆይ! እንደገናም እኔ አገልጋይህ አንድ ነገር እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም “እሺ ተናገሪ” አላት። እርስዋም እንዲህ አለችው፤ “በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ይህን የመሰለ በደል የፈጸምከው ስለምንድን ነው? ልጅህ ከተሰደደበት አገር ተመልሶ እንዲመጣ አልፈቀድክለትም፤ ስለዚህ አሁን በተናገርከው ቃል በራስህ ላይ ፈርደሃል፤ እኛ ሁላችን መሞታችን የማይቀር ነው፤ እኛ በመሬት ላይ እንደ ፈሰሰና ተመልሶም ሊታፈስ እንደማይችል ውሃ ነን፤ እግዚአብሔር ግን በስደት ላይ የሚገኝ ሰው ከእርሱ እንደ ራቀ እንዳይቀር የሚመለስበትን መንገድ ያዘጋጅለታል እንጂ ሕይወቱ በከንቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም። አሁንም ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ወደ አንተ የመጣሁት በዚህ ነገር ሰዎች ያስፈራሩኝ መሆኑን ልነግርህ ነው፤ ‘የጠየቅሁትን ሁሉ ያደርግልኛል’ በሚል ተስፋም በፊትህ ቀርቤአለሁ፤ የምነግርህን አድምጠህ ልጄንና እኔን በማጥፋት እግዚአብሔር የራሱ ካደረገው ምድር ሊያስወግደን ከሚፈልገው ሰው ታድነኛለህ ብዬ አስቤ ነው። እንዲሁም ንጉሥ ሆይ! ንጉሥ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆነና መልካሙን ከክፉው ለይቶ ስለሚያውቅ የተስፋ ቃልህ በሰላም እንድኖር ይረዳኛል ብዬ አስቤ ነው እንግዲህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን!” ንጉሡም “አንድ ጥያቄ እጠይቅሻለሁ፤ አንቺም እውነቱን በሙሉ ንገሪኝ” አላት። እርስዋም “ንጉሥ ሆይ! የፈለግኸውን ጠይቀኝ” አለችው። እርሱም “ይህን እንድታደርጊ ያዘዘሽ ኢዮአብ ነውን?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም እንዲህ ስትል መልስ ሰጠች፤ “ንጉሥ ሆይ! አንተ ከምትለው ሁሉ ፈጽሞ ሊወጣ የሚችል እንደሌለ በአንተ ስም እምላለሁ፤ በእርግጥም ምን ማድረግና ምን ማለት እንዳለብኝ የመከረኝ የአንተ የጦር አዛዥ የሆነው ኢዮዓብ ነው። እርሱም ይህን ያደረገው ነገሮችን ሁሉ ለማስተካከል በማሰብ ነው፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ጥበበኛ ነህ፤ የሚሆነውንም ነገር ሁሉ ታውቃለህ።” ንጉሡም ዘግየት ብሎ ኢዮአብን “ተስማምቼአለሁና ሄደህ ያንን ወጣት አቤሴሎምን ፈልገህ ወደዚህ አምጣው” አለው። ኢዮአብም በዳዊት ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት በአክብሮት ንጉሡን አመሰገነ፤ “የፈለግኹትን እንዳደርግ በመፍቀድህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን አሁን ተረዳሁ” አለ። ተነሥቶም ወደ ገሹር ሄደ፤ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው፤ ይሁን እንጂ ንጉሡ፥ አቤሴሎም በቤተ መንግሥት ውስጥ እንዳይኖር ትእዛዝ ሰጠ፤ ደግሞም ንጉሡ “ከቶ እርሱን ማየት አልፈልግም” አለ። ስለዚህ አቤሴሎም በራሱ ቤት ኖረ፤ ወደ ንጉሡም ፊት ቀርቦ አልታየም። የአቤሴሎምን ያኽል በመልከ መልካምነቱ የታወቀ ሰው በእስራኤል ምድር ከቶ አልነበረም፤ አቤሴሎም ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ ምንም እንከን የሌለበት ሰው ነበር፤ የራሱ ጠጒር እጅግ ብዙ ነበር፤ ስለሚረዝምበትና ስለሚከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ የጠጒሩም ክብደት በቤተ መንግሥት ሚዛን ሲለካ ከሁለት ኪሎ በላይ ነበር። አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ነበሩት፤ የሴት ልጁም ስም ትዕማር ሲሆን እርስዋም እጅግ ውብ ነበረች። አቤሴሎም ንጉሡን ሳያይ በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ኖረ፤ ከዚያን በኋላ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲጠይቅለት ኢዮአብን አስጠራ፤ ኢዮአብ ግን መምጣት አልፈቀደም፤ አቤሴሎም እንደገና ኢዮአብ እንዲመጣለት መልእክት ላከ፤ ኢዮአብ ግን አሁንም ሳይመጣ ቀረ፤ ስለዚህም አቤሴሎም አገልጋዮቹን “ተመልከቱ፤ የኢዮአብ እርሻ ከእኔ እርሻ ቀጥሎ ሲሆን የገብስ ሰብል ይገኝበታል፤ ስለዚህም ሂዱና በእሳት አቃጥሉት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ሄደው ሰብሉን በእሳት አቃጠሉ። ኢዮአብም ወደ አቤሴሎም ቤት ገሥግሦ ሄደና “አገልጋዮችህ የእርሻዬን ሰብል ያቃጠሉት ስለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። አቤሴሎምም “አንተ እኔ ስጠራህ ስላልመጣህ ነው፤ ወደ ንጉሡ ሄደህ ‘ከገሹር ወጥቼ ወደዚህ ለምን መጣሁ? እዚያው ቈይቼ ብሆን ኖሮ በተሻለኝ ነበር’ ብለህ ስለ እኔ ሁኔታ ጠይቅልኝ፤ እንዲሁም ከንጉሡ ጋር መገናኘት እችል ዘንድ ሁኔታዎችን አመቻችልኝ፤ እኔ በደለኛ ሆኜ ከተገኘሁ ሞት ይፍረድብኝ” አለው። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ንጉሥ ዳዊት ሄደና አቤሴሎም ያለውን ሁሉ ነገረው፤ ንጉሡም አቤሴሎምን አስጠራ፤ አቤሴሎምም ሄዶ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም ሳመው።
2 ሳሙኤል 14:1-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ተቆዓ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ኀዘንተኛ በመምሰል የኀዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት ትሆኛለሽ፤ ከዚያም ወደ ንጉሡ ሂጂ፤ እንዲህም በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ መናገር ያለባትን ነገር ነገራት። የተቆዓዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፥ በንጉሡ ፊት በግምባሯ በምድር ላይ ተደፍታ እጅ በመንሣት፥ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች። ንጉሡም፥ “ችግርሽ ምንድነው?” ብሎ ጠየቃት። እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በእርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤ እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፥ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው። እነሆ ዘመዶቼ ሁሉ በአገልጋይህ ላይ ተነሥተው፥ ‘ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፥ ወራሽ እንኳ ብናጠፋ ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለን’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን በማጥፋት፥ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።” ንጉሡም ሴቲቱን፥ “ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ ጉዳይ ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት። ነገር ግን የተቆዓዪቱም ሴት፥ “ንጉሥ ጌታዬ፥ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች። ንጉሡም፥ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አይነካሽም” ሲል መለሰላት። እርሷም፥ “ደም ተበቃዮቹ ተጨማሪ ደም እንዳያፈሱ ልጄም እንዳይገደል፥ ንጉሡ ጌታ አምላኩን ያስብ” አለች። ንጉሡም፥ “ሕያው በሆነው ጌታ እምላለሁ! ከልጅሽ አንድ ጠጉር በምድር ላይ አይወድቅም” አላት። ከዚያም ሴቲቱ፥ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፥ “ተናገሪ” አላት። ሴቲቱም እንዲህ አለችው፥ “አንተስ እንዲህ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ከአገር የተሰደደውን ልጁን ንጉሡ ባለመመለሱ፥ ይህን ሲናገር በራሱ ላይ መፍረዱ አይደለምን? እኛ ሁላችን መሞታችን አይቀሬ ነው፤ በመሬት ላይ እንደ ፈሰሰና ተመልሶም ሊታፈስ እንደማይችል ውሃ ነን፤ እግዚአብሔር የተሰደደ ሰው በስደት በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም። አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤’ ብዬ አሰብሁ፤ ‘እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊያጠፋን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’ አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለሆነ፥ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ከአንተው ጋር ይሁን’ ትላለች።” ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፥ “የምጠይቅሽን ነገር አንድም ሳትደብቂኝ መልሽልኝ” አላት። ሴቲቱም፥ “ንጉሥ ሆይ! ጠይቀኝ” አለችው። ንጉሡም፥ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት። ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። ይህን እንድናገር ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አፍ ያደረገው አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም የነገሩን መልክ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ ያለው ጥበብ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ ስለሚመስል፥ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።” ንጉሡም ኢዮአብን፥ “እነሆ፥ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው። ኢዮአብም መሬት ላይ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባርኮ፥ ኢዮአብ፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የአገልጋይህን ልመና ስለተቀበልከኝ፥ አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቴን ዛሬ ለማወቅ ችያለሁ” አለ። ከዚያም ኢዮአብ ወደ ገሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። ንጉሡ ግን፥ “እዚያው ቤቱ ይሂድ፤ ፊቴን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ ወደ ንጉሡም ፊት ቀርቦ አልታየም። የአቤሴሎምን ያኽል በመልከ መልካምነቱ የታወቀ ሰው በመላው እስራኤል ከቶ አልነበረም፤ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ምንም እንከን የሌለበት ሰው ነበር፤ የራስ ጠጉሩ ሲከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቆርጠው ነበር፤ የተቆረጠውን በሚመዝነው ጊዜ ክብደቱ በቤተ መንግሥት ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ይሆን ነበር። አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የተባለች አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ ሴት ልጁም በጣም ውብ ነበረች። አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ። ከዚያም አቤሴሎም ወደ ንጉሡ እንዲሄድለት ኢዮአብን አስጠራው፤ ኢዮአብ ግን ወደ እርሱ አልመጣም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ላከበት፤ ኢዮአብ ግን አሁንም ሳይመጣ ቀረ። ከዚያም አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ “ተመልከቱ፥ የኢዮአብ እርሻ የሚገኘው ከእኔ እርሻ አጠገብ ነው፤ በእርሻው ላይ የገብስ ሰብል አለው፤ ሄዳችሁም እሳት ልቀቁበት” አላቸው። ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች ሄደው እርሻውን በእሳት አቃጠሉት። ከዚያም ኢዮአብ ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ቤት መጣና፦ “አገልጋዮችህ ለምንድን ነው እርሻዬን ያቃጠሉት?” ብሎ ጠየቀው። አቤሴሎምም፥ ኢዮአብን፥ “‘ከገሹር ለምን መጣሁ? ለእኔ እስካሁንም እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር ብሏል፥’ ብለህ እንድትነግርልኝ ወደ ንጉሡ ልልክህ ወደ እኔ ና ብዬ አስጠራሁህ፤ አሁንም ቢሆን ወደ ንጉሡ ፊት መቅረብ እፈልጋለሁ፤ ምንም ዓይነት በደል ከተገኘብኝ ይግደለኝ” አለው። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ ነገረው። ከዚያም ንጉሡ አቤሴሎምን አስጠራው፤ እርሱም መጥቶ በንጉሡ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።