መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 14
14
1የሶርህያ ልጅ ኢዮአብም የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ ዐወቀ። 2ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና፥ “አልቅሺ፤ የኀዘንም ልብስ ልበሺ፤ ዘይትም አትቀቢ፤ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅስ ሴት ሁኚ፤ 3ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው” አላት፤ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ።
4እንዲሁም የቴቁሔዪቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግንባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፤ ሰግዳም “ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ፤ አድነኝ” አለች። 5ንጉሡም፥ “ምን ሆነሻል?” አላት። እርስዋም አለች፥ “በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ። 6ለእኔም ለአገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ በሜዳም ተጣሉ፤ የሚገላግላቸውም አልነበረም፤ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው። 7እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሡ፤ ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፤ እንዲሁም ደግሞ ለባሌ ስምና ዘር በምድር ላይ እንዳይቀር ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፤”
8ንጉሡም ሴቲቱን፥ “ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ” አላት። 9የቴቁሔዪቱም ሴት ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኀጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን” አለችው። 10ንጉሡም፥ “የሚናገርሽ ማን ነው? አምጪልኝ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም” አለ። 11ያችም ሴት፥ “ለመግደል ባለ ደሞች እንዳይበዙ፤ ልጄንም እንዳይገድሉብኝ ንጉሥ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ያስብ” አለች። እርሱም፥ “የልጅሽስ አንዲት የራሱ ጠጕር በምድር ላይ እንዳትወድቅ ሕያው እግዚአብሔርን” አላት።
12ሴቲቱም፥ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር” አለች፤ እርሱም፥ “ተናገሪ” አላት። 13ሴቲቱም አለች፥ “በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለምን አሰብህ? ወይስ ንጉሥ ያሳደደውን ስላላስመለሰ እንደ በደል ከንጉሥ አፍ ይህ ቃል ወጥቶአልን? 14ሞትን እንሞታለንና፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ እንሆናለንና፥ እግዚአብሔርም ነፍስን ይወስዳል። የተጣለውንም ከእርሱ ያርቅ ዘንድ ያስባል።#ዕብ. “ እግዚአብሔርም የነፍስን ጥፋት አይወድድም ፤ ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ በምክሩ ያስባል” ይላል። 15አሁንም ሕዝቡ ስለሚያዩኝ#ዕብ. “ስለሚያስፈሩኝ” ይላል። ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፤ እኔም አገልጋይህ፦ የእኔን የአገልጋዩን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደ ሆነ ለጌታዬ ለንጉሥ ልናገር፤ 16እኔንና ልጄን ከእግዚአብሔር ርስት ያርቀን ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ አገልጋዩን ይሰማል አልሁ።” 17ያችም ሴት አለች፥ “መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ መሥዋዕትና እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል እንደዚሁ ነው፤ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን።”
18ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ፥ “የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ” አላት። ሴቲቱም፥ “ጌታዬ ንጉሥ ይናገር” አለች። 19ንጉሡም፥ “በዚህ ሁሉ ነገር የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር አለን?” አላት። ሴቲቱም ንጉሡን አለችው፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፤ አገልጋይህ ኢዮአብ አዝዞኛል፤ ይህንም ቃል ሁሉ በአገልጋይህ አፍ አደረገው። 20ይህን ነገር እናገር ዘንድ እንድመጣ ይህን ምክር ያደረገ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። ጌታዬ ግን በዚህ ዓለም የሚደረገውን ሁሉ ታውቅ ዘንድ እንደ መልአከ እግዚአብሔር ጥበብ ጥበበኛ ነህ፤”
21ንጉሡም ኢዮአብን፥ “እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፤ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው” አለው። 22ኢዮአብም በምድር ላይ በግንባሩ ወድቆ ሰገደለት፤ ንጉሡንም አመሰገነ፤ ኢዮአብም፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የአገልጋይህን ነገር አድርገሃልና በዐይንህ ፊት ሞገስን እንዳገኘ አገልጋይህ ዛሬ ዐወቀ” አለ። 23ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌድሶር ሄደ፤ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። 24ንጉሡም፥ “ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ” አለ፤ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም።
25በእስራኤል ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ ያማረ ሰው አልነበረም፤ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም። 26ቀድሞ በመጀመሪያ ዘመን ጠጕሩ ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቈረጠው ነበር፤ ሲቈረጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዝን ነበር። 27ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት። የሴቲቱ ልጅም ስም ትዕማር ይባላል። ያችውም ሴት መልከ መልካም ነበረች፤ እርሷም የሰሎሞን ልጅ የሮብአም ሚስት ሆና አቢያን ወለደችለት።#“እርሷም የሰሎሞን ልጅ የሮብዓም ሚስት ሆና አቢያን ወለደችለት” የሚለው በዕብ. የለም።
28አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም። 29አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፤ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፤ ሁለተኛም ላከበት፤ ሊመጣ ግን አልወደደም። 30አቤሴሎምም ብላቴኖቹን፥ “በእርሻዬ አጠገብ ያለችውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፤ በዚያም ገብስ አለው፤ ሄዳችሁ በእሳት አቃጥሉት” አላቸው። የአቤሴሎምም ብላቴኖች እርሻውን አቃጠሉት። የኢዮአብም አሽከሮች ልብሶቻቸውን ቀድደው ተመልሰው፥ “የአቤሴሎም አሽከሮች እርሻህን በእሳት አቃጠሉት” ብለው ነገሩት።#“የኢዮአብም አሽከሮች ልብሶቻቸውን ቀድደው ተመልሰው የአቤሴሎም አሽከሮች አዝመራህን በእሳት አቃጠሉት ብለው ነገሩት” የሚለው በዕብ. የለም። 31ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና፥ “ብላቴኖችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት?” አለው። 32አቤሴሎምም ኢዮአብን፥ “ከጌድሶር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጬ ቢሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሥ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ና ብዬ ወደ አንተ ላክሁ፤ አሁንም የንጉሡን ፊት አላየሁም፤ ኀጢአት ቢኖርብኝ ይግደለኝ” አለው። 33ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፤ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ ሰገደለት፤ በንጉሡም ፊት ወደ ምድር በግንባሩ ወደቀ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ