2 ነገሥት 22:1-20
2 ነገሥት 22:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ከባሱሮት የሆነ የአዳያ ልጅ ይዲያ ነበረች። በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ቀኝም ግራም አላለም። በንጉሡም በኢዮስያስ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመተ መንግሥት በስምንተኛው ወር ንጉሡ የእግዚአብሔርን ቤት ጸሓፊ የሜሱላምን ልጅ የኤሴልዩን ልጅ ሳፋንን እንዲህ ሲል ላከው፦ “ወደ ታላቁ ካህን ወደ ኬልቅዩ ወጥተህ ደጃፉን የሚጠብቁ ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን ወርቅ ቍጠር። በእግዚአብሔርም ቤት ላሉት ሠራተኞች አለቆች ይስጡት፤ እነርሱም የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚጠግኑት ሠራተኞች፥ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች፥ ለድንጋይም ወቃሪዎች፥ መቅደሱንም ለመጠገን እንጨትንና የተወቀረውን ድንጋይ ለሚገዙ ይክፈሉት።” ነገር ግን እነርሱ በእምነት ይሠሩ ነበርና የሰጡአቸውን ገንዘብ አይቈጣጠሩአቸውም ነበር። ታላቁ ካህንም ኬልቅያስ ጸሓፊውን ሳፋንን፥ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ” አለው፤ ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፥ እርሱም አነበበው። ጸሓፊውም ሳፋን ወደ ንጉሡ መጣ፤ ለንጉሡም፥ “በመቅደሱ የተገኘውን ገንዘብ አገልጋዮችህ አፈሰሱት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ሥራ ለመሥራት ለተመደቡት ሰዎች ሰጡት” ብሎ ነገረው። ጸሓፊው ሳፋንም ለንጉሡ፥ “ካህኑ ኬልቅያስ የሕግ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ንጉሡም ካህኑን ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክዩንም ልጅ ዓክቦርን፥ ጸሓፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓስያን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ ስለዚችም ስለተገኘችው መጽሐፍ ቃል ሁሉ እግዚአብሔርን ጠይቁ። እንዲሁም ካህኑ ኬልቅያስና አኪቃም ዓክቦርም ሳፋንና ዓሳያም ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሓስራ ልጅ ወደ ቴቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢዪቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በዚያ በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ለእርስዋም ነገሩአት። እርስዋም አለቻቸው፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የይሁዳ ንጉሥ እንዳነበበው እንደዚህ መጽሐፍ ቃል ሁሉ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ። በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ታስቈጡኝ ዘንድ ትታችሁኛልና፥ ለሌሎች አማልክትም ዐጥናችኋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃል፥ ልብህን አላደነደንህምና፥ እነርሱም ለጥፋትና ለመርገም እንዲሆኑ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፥ ልብስህን ቀድደሃልና፥ በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር። ነገሩ እንደዚህ አይደለም፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ዐይኖችህ አያዩም።” ይህንም ለንጉሡ ነገሩት።
2 ነገሥት 22:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም የቦጽቃት አገር ሰው የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ። በዘመነ መንግሥቱ በዐሥራ ስምንተኛውም ዓመት ኢዮስያስ የሜሶላምን የልጅ ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ጸሓፊውን ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላከው፤ እንዲህም አለው፤ “ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ ውጣ፤ የበር ጠባቂዎች ከሕዝቡ ሰብስበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባው ገንዘብ ምን ያህል እንደ ሆነ ራሱ እንዲቈጥረው አድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚያድሱት ይክፈሏቸው፤ የሚከፍሉትም ለየእጅ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ ዕድሳት ሥራ የሚሆኑ ዕንጨቶችና ጥርብ ድንጋዮች ይግዙበት። ሰዎቹ ታማኞች ስለ ሆኑም የተሰጣቸውን ገንዘብ መቈጣጠር አያስፈልግም።” ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ እኮ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” ብሎ ሰጠው፤ እርሱም ተቀብሎ አነበበው። ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ሄዶ ንጉሡን እንዲህ አለው፣ “ሹማምትህ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተው ቤተ መቅደሱን እየተቈጣጠሩ ለሚያሠሩት አስረክበዋል።” ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ለንጉሡ፣ “ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” ብሎ ነገረው። ሳፋንም ለንጉሡ ከመጽሐፉ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ። ከዚያም ንጉሡ ካህኑን ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓክቦርን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ሂዱና ስለ እኔ፣ ስለ ሕዝቡና ስለ ይሁዳም ሁሉ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ለዚህ መጽሐፍ ቃል ባለመታዘዛቸው፣ እኛን በተመለከተም በዚሁ ላይ የተጻፈውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፣ በእኛ ላይ የነደደው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና።” ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦርና፣ ሳፋን፣ ዓሳያም የሐርሐስ የልጅ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የአልባሳት ጠባቂውን የሴሌምን ሚስት ነቢዪቱን ሕልዳናን ለመጠየቅ ሄዱ። እርሷም ምክር በጠየቋት ቦታ፣ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው የከተማው ክፍል ትኖር ነበር። ነቢዪቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ የተጻፈውን ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎቹ ላይ አመጣለሁ። እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና በእጆቻቸው ሥራ ሁሉ ለቍጣ ስላነሣሡኝ፣ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ለርግማንና ለጥፋት የተዳረጉ ስለ መሆናቸው በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገርኩትን በሰማህ ጊዜ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔር ፊት ራስህን ስላዋረድህ፣ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ ስላለቀስህ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ፣ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ሰዎቹም መልሷን ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።
2 ነገሥት 22:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ከባሱሮት የሆነ የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች። በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ቀኝም ግራም አላለም። በንጉሡም በኢዮስያስ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር ንጉሡ ጸሐፊውን የሜሶላምን ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤት ላከው፤ እንዲህም አለው “የመቅደሱ በረኞች ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን ገንዘብ ይደምር ዘንድ ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ኬልቅያስ ሂድ። በእግዚአብሔርም ቤት ላሉት ሠራተኞች አለቆች ይስጡት፤ እነርሱም የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚጠግኑት ሠራተኞች፥ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች፥ ለድንጋይ ወቃሪዎችም፥ መቅደሱንም ለመጠገን እንጨትንና የተወቀረውን ድንጋይ ለሚገዙ ይክፈሉት። ነገር ግን እነርሱ የታመኑ ስለሆኑ በእጃቸው ስለ ተሰጠው ገንዘብ አይቈጣጠሩአቸው።” ካህኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ፤” አለው፤ ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፤ እርሱም አነበበው። ጸሐፊው ሳፋንም ወደ ንጉሡ መጣ፤ ለንጉሡም “በመቅደሱ የተገኘውን ገንዘብ ባሪያዎችህ አፈሰሱት “በእግዚአብሔርም ቤት ሠራተኞች ላይ ለተሾሙት አለቆች ሰጡት፤” ብሎ አወራለት። ጸሐፊው ሳፋንም ለንጉሡ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል፤” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ንጉሡም ካህኑን ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓክቦርን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን “አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ የዚህችን የተገኘችውን መጽሐፍ ቃል እግዚአብሔርን ጠይቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁም ካህኑ ኬልቅያስና አኪቃም ዓክቦርም ሳፋንና ዓሳያም ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢያቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ከእርስዋም ጋር ተነጋገሩ። እርስዋም አለቻቸው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እነሆ፥ የይሁዳ ንጉሥ እንዳነበበው እንደ መጽሐፉ ቃል ሁሉ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ። በእጃቸው ሥራ ሁሉ ያስቈጡኝ ዘንድ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት ‘የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ስለ ሰማኸው ቃል፥ ልብህ ገር ሆኖአልና፥ እነርሱም ለድንቅና ለመርገም እንዲሆኑ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፥ ልብስህን ቀድደሃልና፥ በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህም ደግሞ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራ ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ዐይኖችህ አያዩም።’” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።
2 ነገሥት 22:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይዲዳ ተብላ የምትጠራ የቦጽቃት ከተማ ተወላጅ የሆነው የዐዳያ ልጅ ነበረች፤ ኢዮስያስ የቀድሞ አባቱን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተልና ለእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ታዛዥ በመሆን፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የመሹላም የልጅ ልጅ፥ የአጻልያ ልጅ የሆነውን የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ሳፋንን ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ወደ ቤተ መቅደስ ላከው፤ “ሒልቂያ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ሊቀ ካህናቱ ሂድ፤ ወደ ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በር አጠገብ በየተራ ከሕዝቡ ገንዘብ የመሰብሰብ ኀላፊነት የተሰጣቸው ካህናት እስከ አሁን ምን ያኽል ገንዘብ እንደ ሰበሰቡ የሚገልጥ የሒሳብ ማስረጃ ይዘህ ና፤ የመቅደሱን እድሳት ለመቈጣጠር ለተሾሙት ሰዎች ያስረክቡ፤ እነርሱም የተረከቡትን ገንዘብ ቤተ መቅደሱን ለሚጠግኑ፥ ለአናጢዎች፥ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይክፈሉ፤ እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሳንቃዎችንና የተጠረቡ ድንጋዮችን ይግዙ፤ የሥራው ኀላፊዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ሆኑ እነርሱን ስለ ገንዘቡ አወጣጥ መቈጣጠር አያስፈልግም።” ከዚህ በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ከንጉሡ የተላከውን ትእዛዝ ለሒልቂያ ሰጠ፤ ሒልቂያም “የሕጉን መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘሁ” ብሎ ለሳፋን ሰጠው፤ ሳፋንም ተቀብሎ አነበበው፤ ከዚያም በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ወደ ንጉሡ ተመልሶ ሄደና “አገልጋዮችህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተቀብለው ለእድሳቱ ሥራ ኀላፊዎች ለሆኑት ሰዎች አስረክበዋል” ሲል አስረዳ፤ ከዚያም ቀጠል በማድረግ፥ “ካህኑ ሒልቂያ አግኝቶ የሰጠኝ መጽሐፍ ይኸው” ብሎ ለንጉሡ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ወዲያውኑ ለካህኑ ለሒልቂያ፥ የሳፋን ልጅ ለሆነው ለአሒቃም፥ የሚካያ ልጅ ለሆነው ለዐክቦር፥ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሆነው ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፤ “እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቈጥቶአል።” ሒልቂያ፥ አሒቃም፥ ዐክቦር፥ ሳፋንና ዐሣያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሑልዳ ተብላ የምትጠራውን ነቢይት ለመጠየቅ ሄዱ፤ የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው ባልዋ ሻሉም የቤተ መቅደስ አልባሳት ኀላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት። እርስዋም እንዲህ አለቻቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዚህች ቦታና በሕዝብዋ ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ። እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ በእጃቸው በሠሩአቸው ጣዖቶች ሁሉ እኔን አስቈጥተውኛል፤ ቊጣዬም አይበርድም፤ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተህ፥ ይህችን ቦታና ሕዝብዋን የተረገሙና ባድማ እንደማደርግ የተናገርኩትን ቃል በሰማህ ጊዜ ልብህ ተነክቶ ራስህን በማዋረድ፥ ልብስህን በመቅደድና በፊቴም በማልቀስህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ። ከዚህም የተነሣ በኢየሩሳሌም ላይ የማመጣው ቅጣት አንተ በዐይንህ ሳታየው እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህም አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’ ” ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ።
2 ነገሥት 22:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይዲዳ ተብላ የምትጠራ የቦጽቃት ከተማ ተወላጅ የሆነው የዐዳያ ልጅ ነበረች፤ ኢዮስያስ የቀድሞ አባቱን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተልና ለእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ታዛዥ በመሆን፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የመሹላም የልጅ ልጅ፥ የአጻልያ ልጅ የሆነውን የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ሳፋንን ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ወደ ቤተ መቅደስ ላከው፤ “ሒልቂያ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ሊቀ ካህናቱ ሂድ፤ ወደ ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በር አጠገብ በየተራ ከሕዝቡ ገንዘብ የመሰብሰብ ኃላፊነት የተሰጣቸው ካህናት እስከ አሁን ምን ያኽል ገንዘብ እንደ ሰበሰቡ የሚገልጥ የሒሳብ ማስረጃ ይዘህ ና፤ ይህም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም የጌታን ቤተ መቅደስ ለሚያ ድሱት ይክፈሏቸው፤ የሚከፍሉትም ለአና ጺዎች፥ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ የሚሆኑ ሳንቃዎችና የተጠረቡ ድንጋዮች ይግዙበት። የሥራው ኃላፊዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ሆኑ እነርሱን ስለ ገንዘቡ አወጣጥ መቆጣጠር አያስፈልግም።” ከዚህ በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ከንጉሡ የተላከውን ትእዛዝ ለሒልቂያ ሰጠ፤ ሒልቂያም “የሕጉን መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘሁ” ብሎ ለሳፋን ሰጠው፤ ሳፋንም ተቀብሎ አነበበው፤ ከዚያም በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ወደ ንጉሡ ተመልሶ ሄደና “አገልጋዮችህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተቀብለው ለእድሳቱ ሥራ ኃላፊዎች ለሆኑት ሰዎች አስረክበዋል” ሲል አስረዳ፤ ከዚያም ቀጠል በማድረግ፥ “ካህኑ ሒልቂያ አግኝቶ የሰጠኝ መጽሐፍ ይኸው” ብሎ ለንጉሡ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማ ጊዜ በኀዘን ልብሱን ቀደደ፤ ወዲያውኑ ለካህኑ ለሒልቂያ፥ የሳፋን ልጅ ለሆነው ለአሒቃም፥ የሚካያ ልጅ ለሆነው ለዐክቦር፥ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሆነው ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፤ “እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቆጥቶአል።” ሒልቂያ፥ አሒቃም፥ ዐክቦር፥ ሳፋንና ዐሣያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሑልዳ ተብላ የምትጠራውን ነቢይት ለመጠየቅ ሄዱ፤ የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው ባሏ ሻሉም የቤተ መቅደስ አልባሳት ኃላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት። እርሷም እንዲህ አለቻቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዚህች ቦታና በሕዝብዋ ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ። እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ በእጃቸው በሠሩአቸው ጣዖቶች ሁሉ እኔን አስቆጥተውኛል፤ ቁጣዬም አይበርድም፤ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተህ፥ ይህችን ቦታና ሕዝብዋን የተረገሙና ባድማ እንደማደርግ የተናገርኩትን ቃል በሰማህ ጊዜ ልብህ ተነክቶ ራስህን በማዋረድ፥ ልብስህን በመቅደድና በፊቴም በማልቀስህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ። ከዚህም የተነሣ በኢየሩሳሌም ላይ የማመጣው ቅጣት አንተ በዐይንህ ሳታየው እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህም አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’” ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ።