የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 22

22
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ
(2ዜ.መ. 34፥1-2)
1ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይዲዳ ተብላ የምትጠራ የቦጽቃት ከተማ ተወላጅ የሆነው የዐዳያ ልጅ ነበረች፤ #ኤር. 3፥6። 2ኢዮስያስ የቀድሞ አባቱን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተልና ለእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ታዛዥ በመሆን፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ።
የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ መገኘት
(2ዜ.መ. 34፥8-28)
3ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የመሹላም የልጅ ልጅ፥ የአጻልያ ልጅ የሆነውን የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ሳፋንን ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ወደ ቤተ መቅደስ ላከው፤ 4“ሒልቂያ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ሊቀ ካህናቱ ሂድ፤ ወደ ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በር አጠገብ በየተራ ከሕዝቡ ገንዘብ የመሰብሰብ ኀላፊነት የተሰጣቸው ካህናት እስከ አሁን ምን ያኽል ገንዘብ እንደ ሰበሰቡ የሚገልጥ የሒሳብ ማስረጃ ይዘህ ና፤ 5-6የመቅደሱን እድሳት ለመቈጣጠር ለተሾሙት ሰዎች ያስረክቡ፤ እነርሱም የተረከቡትን ገንዘብ ቤተ መቅደሱን ለሚጠግኑ፥ ለአናጢዎች፥ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይክፈሉ፤ እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሳንቃዎችንና የተጠረቡ ድንጋዮችን ይግዙ፤ 7የሥራው ኀላፊዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ሆኑ እነርሱን ስለ ገንዘቡ አወጣጥ መቈጣጠር አያስፈልግም።” #2ነገ. 12፥15።
8ከዚህ በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ከንጉሡ የተላከውን ትእዛዝ ለሒልቂያ ሰጠ፤ ሒልቂያም “የሕጉን መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘሁ” ብሎ ለሳፋን ሰጠው፤ ሳፋንም ተቀብሎ አነበበው፤ 9ከዚያም በኋላ ጸሐፊው ሳፋን ወደ ንጉሡ ተመልሶ ሄደና “አገልጋዮችህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተቀብለው ለእድሳቱ ሥራ ኀላፊዎች ለሆኑት ሰዎች አስረክበዋል” ሲል አስረዳ፤ 10ከዚያም ቀጠል በማድረግ፥ “ካህኑ ሒልቂያ አግኝቶ የሰጠኝ መጽሐፍ ይኸው” ብሎ ለንጉሡ አነበበለት።
11ንጉሡም የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ 12ወዲያውኑ ለካህኑ ለሒልቂያ፥ የሳፋን ልጅ ለሆነው ለአሒቃም፥ የሚካያ ልጅ ለሆነው ለዐክቦር፥ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሆነው ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፤ 13“እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቈጥቶአል።”
14ሒልቂያ፥ አሒቃም፥ ዐክቦር፥ ሳፋንና ዐሣያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሑልዳ ተብላ የምትጠራውን ነቢይት ለመጠየቅ ሄዱ፤ የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው ባልዋ ሻሉም የቤተ መቅደስ አልባሳት ኀላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት። 15እርስዋም እንዲህ አለቻቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ 16“እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዚህች ቦታና በሕዝብዋ ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ። 17እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ በእጃቸው በሠሩአቸው ጣዖቶች ሁሉ እኔን አስቈጥተውኛል፤ ቊጣዬም አይበርድም፤ 18እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተህ፥ 19ይህችን ቦታና ሕዝብዋን የተረገሙና ባድማ እንደማደርግ የተናገርኩትን ቃል በሰማህ ጊዜ ልብህ ተነክቶ ራስህን በማዋረድ፥ ልብስህን በመቅደድና በፊቴም በማልቀስህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ። 20ከዚህም የተነሣ በኢየሩሳሌም ላይ የማመጣው ቅጣት አንተ በዐይንህ ሳታየው እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህም አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’ ”
ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ