ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 23
23
ኢዮስያስ አረማዊ አምልኮን ማስወገዱ
(2ዜ.መ. 34፥3-7፤29-33)
1ንጉሥ ኢዮስያስ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን የታወቁ ሽማግሌዎች ሁሉ ጠራ፤ 2እነርሱም ካህናት፥ ነቢያት፥ ሌሎችም ሰዎች ከታናሾች ጀምሮ እስከ ታላቆች ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ ንጉሡም በዚያ ጠፍቶ በነበረውና በቤተ መቅደስ በተገኘው መጽሐፍ የሰፈረውን ቃል በሙሉ ለሕዝቡ አነበበ፤ 3ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ በሙሉ ልቡና ሓሳቡ እግዚአብሔርን ለመከተልና ትእዛዞቹን፥ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን ለመጠበቅ በእርሱ ፊት ቃል ኪዳኑን አደሰ፤ ስለዚህም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ቃል ኪዳን አረጋገጠ፤ ሕዝቡም በቃል ኪዳኑ ተባበረ።
4ከዚህም በኋላ ኢዮስያስ ሊቀ ካህናቱን ሒልቅያን፥ ረዳቶቹ የሆኑትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን መግቢያ በር ዘብ የሚጠብቁ ተረኞችን ጠርቶ ለባዓልና አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ፥ እንዲሁም ለከዋክብት ማምለኪያ ያገለግሉ የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ንጉሡም እነዚያን ዕቃዎች ሁሉ ከኢየሩሳሌም ውጪ ባለው በቄድሮን ሸለቆ በእሳት አቃጥሎ ዐመዱን ወደ ቤትኤል ወሰደው፤ 5በይሁዳ ከተማዎችና በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ባሉት ስፍራዎች ሁሉ በየኰረብታው ላይ በነበሩት መሠዊያዎች መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ የይሁዳ ነገሥታት ሾመዋቸው የነበሩትን ካህናት ሁሉ ከሥራ አሰናበተ፤ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ፥ ለፀሐይ፥ ለጨረቃ፥ ፀሐይን ለሚዞሩ ዓለማትና ለከዋክብት መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉ ካህናትን ሁሉ ሻረ፤ 6አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ከቤተ መቅደስ ነቅሎ ከከተማይቱ በማውጣት ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ትቢያ እስኪሆንም አድቅቆ፥ በሕዝብ መቃብር ላይ በተነው። #2ነገ. 21፥3፤ 2ዜ.መ. 33፥3። 7ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶች በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉበትንና ሴቶችም አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ መጋረጃ የሚፈትሉበትን ክፍል ሁሉ ደመሰሰ። 8በይሁዳ ከተሞችና በመላ ሀገሪቱ ከገባዕ እስከ ቤርሳቤህ የነበሩትን ካህናት ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፤ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ርኩስ መሆናቸውን ዐወጀ፤ እንዲሁም የከተማይቱ ገዢ ኢያሱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ከዋናው ቅጽር በር በስተ ግራ በኩል ባሠራው ቅጽር በር አጠገብ የሚገኙትን መስገጃዎች አፈራረሰ። 9እነዚያም ካህናት በቤተ መቅደስ ከማገልገል ታገዱ፤ ይሁን እንጂ ለጓደኞቻቸው ካህናት ይሰጥ የነበረውን እርሾ ያልነካው ኅብስት እንዲመገቡ ተፈቅዶላቸው ነበር።
10ንጉሥ ኢዮስያስ በሒኖም ሸለቆ የነበረው “ቶፌት” ተብሎ የሚጠራው የአሕዛብ ማምለኪያ ቦታ የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ከዚህም የተነሣ “ሞሌክ” ተብሎ ለሚጠራው አምላክ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ ማንም እንዳይኖር ተከለከለ፤ #ዘሌ. 18፥21፤ ኤር. 19፥1-6፤ 32፥35። 11የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ አምልኮ መድበዋቸው የነበሩትን ፈረሶች ሁሉ አስወገደ፤ ለዚሁ አምልኮ የሚያገለግሉ የነበሩትን ሠረገሎች አቃጠለ፤ እነዚህ ሁሉ ቀደም ሲል ታላቁ ባለሥልጣን ናታን ሜሌክ በሚኖርባቸው ክፍሎች አጠገብና በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቅጽር በር አጠገብ ይገኙ ነበር፤ 12ንጉሥ አካዝ ባሠራቸው መኖሪያ ክፍሎች ጣራ ላይ በሚገኘው ቤተ መንግሥት የይሁዳ ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን መሠዊያዎችና በቤተ መቅደሱ ሁለት አደባባዮች ንጉሥ ምናሴ አሠርቶአቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ኢዮስያስ ደመሰሳቸው፤ መሠዊያዎቹንም አንከታክቶ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ ጣላቸው። #2ነገ. 21፥5፤ 2ዜ.መ. 33፥5። 13እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ከርኲሰት ተራራ በስተ ደቡብ ዐስታሮት ተብላ ለምትጠራው ለሲዶና አምላክ፥ ከሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞአብ አምላክና ሞሌክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞን አምላክ ንጉሥ ሰሎሞን አሠርቶአቸው የነበሩት አጸያፊዎች ምስሎች ሁሉ የረከሱ መሆናቸውን አስገነዘበ። #1ነገ. 11፥7። 14ንጉሥ ኢዮስያስ የድንጋይ ዐምዶችን ሁሉ ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስሎች አንከታክቶ ጣለ፤ እነርሱ ቆመውበት የነበረውንም ስፍራ የሙታን አጥንት ሞላበት።
15እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤትኤል አሠርቶት የነበረውን የማምለኪያ ቦታ ኢዮስያስ አፈራርሶ ጣለ፤ መሠዊያውን ነቅሎ፥ የተሠራበትን ድንጋይ ሁሉ ሰባብሮ በማድቀቅ እንደ ትቢያ አደረገው፤ የአሼራንም ምስል በእሳት አቃጠለ፤ 16ከዚህም በኋላ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት፥ በኰረብቶች ላይ የተሠሩ መቃብሮችን አየ፤ በእነዚያም መቃብሮች ውስጥ የነበረውን ዐፅም ሁሉ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በእሳት አቃጠለው፤ በዚህም ዐይነት መሠዊያው የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ኢዮስያስ ይህንን ሁሉ በማድረጉ ከብዙ ጊዜ በፊት በተደረገ የአምልኮ በዓል ላይ ንጉሥ ኢዮርብዓም በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ ነቢዩ የተናገረው የትንቢት ቃል ተፈጸመ፤ ንጉሥ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት ይህን ትንቢት ተናግሮ የነበረው ነቢይ የተቀበረበትን መካነ መቃብር አይቶ፥ #1ነገ. 13፥2። 17“ያ መቃብር የማን ነው?” ሲል ጠየቀ።
የቤትኤልም ሕዝብ “ከይሁዳ መጥቶ በዚህ መሠዊያ ላይ ይህን አንተ ያደረግኸው ነገር ሁሉ እንደሚፈጸምበት ተናግሮ የነበረው የነቢዩ መቃብር ነው” ሲሉ መለሱለት። #1ነገ. 13፥30-32።
18ኢዮስያስም “እንዳለ ይኑር፤ ተዉት፤ የእርሱ ዐፅም ከዚህ መንቀሳቀስ የለበትም!” ሲል መለሰ።
ስለዚህም የእርሱም ሆነ የሰማርያው ነቢይ ዐፅሞች ከዚያ እንዲነሡ አልተደረገም።
19ንጉሥ ኢዮስያስ በማንኛይቱም የእስራኤል ከተማ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን የእግዚአብሔርን ቊጣ ለማነሣሣት ምክንያት የሆኑትን የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሁሉ አፈራረሰ፤ በቤትኤል ያደረገውን ሁሉ በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ፈጸመ፤ 20በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ያገለግሉ የነበሩትንም አሕዛብ ካህናትን ገደለ፤ በመሠዊያዎቹም ላይ አጥንት አቃጠለባቸው። ይህን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
ኢዮስያስ የፋሲካን በዓል ማክበሩ
(2ዜ.መ. 35፥1-19)
21ንጉሥ ኢዮስያስ በቃል ኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የፋሲካን በዓል ያከብሩ ዘንድ ሕዝቡን አዘዘ። 22መሳፍንት የሕዝቡ ገዢዎች ከነበሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን በማንኛዎቹም የእስራኤል ወይም የይሁዳ ነገሥታት አማካይነት ይህን የመሰለ የፋሲካ በዓል ተከብሮ አያውቅም። 23ይሁን እንጂ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ተከበረ።
ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ለውጥ
24ሊቀ ካህናቱ ሒልቂያ በቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው ሕግ ሁሉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በማሰብ፥ ንጉሥ ኢዮስያስ ከኢየሩሳሌምና ከሌላውም የይሁዳ ከተማ ሁሉ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ሁሉ የቤተሰብ አማልክትን፥ ጣዖቶችንና ሌሎችንም አረማዊ የአምልኮ መፈጸሚያ ዕቃዎችን ሁሉ አስወገደ። 25ለኦሪት ሕግ በመታዘዝ በፍጹም ልቡ፥ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ኀይሉ እግዚአብሔርን ያገለገለ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ ከእርሱም በፊት ሆነ ከእርሱ ወዲህ ከቶ አልነበረም።
26ነገር ግን ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ምናሴ ባደረገው ክፉ ነገር ምክንያት በይሁዳ ላይ የነደደው አስፈሪ የእግዚአብሔር ቊጣ እስከ አሁን ድረስ ገና አልበረደም ነበር። 27ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “በእስራኤል ላይ ያደረግኹትን ነገር ሁሉ በይሁዳም ላይ አደርጋለሁ፤ ይኸውም የይሁዳን ሕዝብ ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኳትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና ስሜ በዚያ ይጠራል ብዬ የነበረውንም ቤተ መቅደስ እተዋለሁ።”
የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(2ዜ.መ. 35፥20—36፥1)
28ንጉሥ ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 29በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ነኮ የተባለው የግብጽ ንጉሥ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመርዳት ሠራዊቱን እየመራ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተጓዘ፤ ንጉሥ ኢዮስያስም መጊዶ ላይ የግብጽን ሠራዊት ለማገድ ጦርነት ገጥሞ በዚያ ውጊያ ላይ ተገደለ፤ 30ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው እዚያ በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ።
የይሁዳም ሰዎችም የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአካዝን መረጡ፤ ቀብተውም አነገሡት።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአካዝ
(2ዜ.መ. 36፥2-4)
31ኢዮአካዝ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ ሦስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም ሐሙጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፤ 32ኢዮአካዝም የቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 33እርሱንም ኒካዑ ተብሎ የሚጠራው የግብጽ ንጉሥ ኢዮአካዝ በኢየሩሳሌም እንዳይነግሥ በሐማት ምድር በምትገኘው በሪብላ እስረኛ በማድረግ፥ ይሁዳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ብር፥ ሠላሳ አራት ኪሎ ወርቅ ግብር እንዲከፍል ባደረገው ጊዜ የኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ሆነ። 34ንጉሥ ኒካዑ የኢዮስያስ ልጅ ኤልያቄም በአባቱ በኢዮስያስ እግር ተተክቶ በይሁዳ እንዲነግሥ አደረገ፤ ስሙንም በመለወጥ ኢዮአቄም ብሎ ጠራው፤ ኢዮአሐዝም በንጉሥ ነኮ ተማርኮ ወደ ግብጽ ተወሰደ፤ በዚያም ሞተ። #ኤር. 22፥11-12።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም
(2ዜ.መ. 36፥5-8)
35ኢዮአቄም ንጉሥ ነኮ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፤ ይህንንም ለማድረግ እንድየችሎታው በሕዝቡ ላይ ግብር ጣለ።
36ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ዘቢዳ ተብላ የምትጠራ የሩማ ከተማ ተወላጅ የሆነው የፐዳያ ልጅ ነበረች። #ኤር. 22፥18-19፤ 26፥1-6፤ 35፥1-19። 37ኢዮአቄም የቀድሞ አባቶቹ እንደ አደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 23: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997