2 ነገሥት 22
22
የሕጉ መጽሐፍ ተገኘ
22፥1-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 34፥1-2፡8-28
1ኢዮስያስ ሲነግሥ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም የባሱሮት አገር ሰው የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች። 2ኢዮስያስም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ አባቱ ዳዊት በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ።
3በዘመነ መንግሥቱ በዐሥራ ስምንተኛውም ዓመት ኢዮስያስ የሜሶላምን የልጅ ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ጸሓፊውን ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላከው፤ እንዲህም አለው፤ 4“ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ ውጣ፤ የበር ጠባቂዎች ከሕዝቡ ሰብስበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባው ገንዘብ ምን ያህል እንደ ሆነ ራሱ እንዲቈጥረው አድርግ፤ 5ይህም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚያድሱት ይክፈሏቸው፤ 6የሚከፍሉትም ለዐናጺዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ የሚሆኑ ሳንቃዎችና የተጠረቡ ድንጋዮች ይግዙበት። 7ሰዎቹ ታማኞች ስለ ሆኑም የተሰጣቸውን ገንዘብ መቈጣጠር አያስፈልግም።”
8ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ እኮ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” ብሎ ሰጠው፤ እርሱም ተቀብሎ አነበበው። 9ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ሄዶ ለንጉሡ፣ “ሹማምትህ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተዋል፤ ቤተ መቅደሱን እየተቈጣጠሩ ለሚያሠሩትም አስረክበዋል” አለው። 10ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ለንጉሡ፣ “ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” ብሎ ነገረው። ሳፋንም ለንጉሡ ከመጽሐፉ አነበበለት።
11ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ። 12ከዚያም ካህኑን ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓክቦርን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ 13“ሂዱና ስለ እኔ፣ ስለ ሕዝቡና ስለ ይሁዳም ሁሉ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ምን እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ለዚህ መጽሐፍ ቃል ባለመታዘዛቸው፣ እኛን በተመለከተም በዚሁ ላይ የተጻፈውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፣ በእኛ ላይ የሚነድደው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና።”
14ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦርና፣ ሳፋን፣ ዓሳያም የሐርሐስ የልጅ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የአልባሳት ጠባቂውን የሴሌምን ሚስት ነቢዪቱን ሕልዳናን ለመጠየቅ ሄዱ። እርሷም የምትኖረው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ሰፈር ነበር።
15ነቢዪቱም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ 16እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ አመጣለሁ። 17እኔን ስለተውኝና ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው በሠሯቸውም አማልክት ሁሉ#22፥17 ወይም፣ በሠሩት ሥራ ሁሉ ስላስቈጡኝ፣ ቍጣዬ በዚህ ቦታ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ 18እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ይህን ንገሩት፤ ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ 19‘ለርግማንና ለጥፋት የተዳረጉ ስለ መሆናቸው በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ የተናገርኩትን ስትሰማ ልብህ ስለ ተነካና ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ስላዋረድህ፣ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ ስላለቀስህ እግዚአብሔር ሰምቼሃለሁ ብሏል። 20ስለዚህ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ ወደ መቃብር በሰላም ትወርዳለህ፤ በዚህ ቦታም የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ”
ሰዎቹም መልሱን ለንጉሡ ይዘውለት ሄዱ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 22: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.