ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 22
22
ኢዮስያስ በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 34፥1-2)
1ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ከባሱሮት የሆነ የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች። 2በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ቀኝም ግራም አላለም።
የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ መገኘት
(2ዜ.መ. 34፥8-28)
3በንጉሡም በኢዮስያስ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር ንጉሡ ጸሐፊውን የሜሶላምን ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤት ላከው፤ እንዲህም አለው 4“የመቅደሱ በረኞች ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን ገንዘብ ይደምር ዘንድ ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ኬልቅያስ ሂድ። 5በእግዚአብሔርም ቤት ላሉት ሠራተኞች አለቆች ይስጡት፤ እነርሱም የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚጠግኑት ሠራተኞች፥ 6ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች፥ ለድንጋይ ወቃሪዎችም፥ መቅደሱንም ለመጠገን እንጨትንና የተወቀረውን ድንጋይ ለሚገዙ ይክፈሉት። 7ነገር ግን እነርሱ የታመኑ ስለሆኑ በእጃቸው ስለ ተሰጠው ገንዘብ አይቈጣጠሩአቸው።”
8ካህኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ፤” አለው፤ ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፤ እርሱም አነበበው። 9ጸሐፊው ሳፋንም ወደ ንጉሡ መጣ፤ ለንጉሡም “በመቅደሱ የተገኘውን ገንዘብ ባሪያዎችህ አፈሰሱት “በእግዚአብሔርም ቤት ሠራተኞች ላይ ለተሾሙት አለቆች ሰጡት፤” ብሎ አወራለት። 10ጸሐፊው ሳፋንም ለንጉሡ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል፤” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። 11ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 12ንጉሡም ካህኑን ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓክቦርን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን 13“አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ የዚህችን የተገኘችውን መጽሐፍ ቃል እግዚአብሔርን ጠይቁ፤” ብሎ አዘዛቸው።
14እንዲሁም ካህኑ ኬልቅያስና አኪቃም ዓክቦርም ሳፋንና ዓሳያም ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢያቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ከእርስዋም ጋር ተነጋገሩ። 15እርስዋም አለቻቸው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት 16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እነሆ፥ የይሁዳ ንጉሥ እንዳነበበው እንደ መጽሐፉ ቃል ሁሉ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ። 17በእጃቸው ሥራ ሁሉ ያስቈጡኝ ዘንድ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ 18እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት ‘የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ስለ ሰማኸው ቃል፥ ልብህ ገር ሆኖአልና፥ 19እነርሱም ለድንቅና ለመርገም እንዲሆኑ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፥ ልብስህን ቀድደሃልና፥ በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። 20ስለዚህም ደግሞ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራ ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ዐይኖችህ አያዩም።’” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 22: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ