2 ነገሥት 2:1-11
2 ነገሥት 2:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልገላ ተነሥተው ይጓዙ ነበር። ኤልያስም ኤልሳዕን፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ቤቴል ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው። ኤልሳዕ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” አለው። ስለዚህ ዐብረው ወደ ቤቴል ወረዱ። በቤቴል የነበሩ የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። ኤልሳዕም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” አለ። ከዚያም ኤልያስ፣ “ኤልሳዕ ሆይ፤ እግዚአብሔር እኔን ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው። እርሱም፤ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ዐብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ። በኢያሪኮ የነበሩትም የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። እርሱም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰ። ከዚያም ኤልያስ፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና አንተ እዚሁ ቈይ” አለው። እርሱም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ሁለቱም ዐብረው ሄዱ። ከነቢያትም ማኅበር ዐምሳው ሄደው፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከቆሙበት ከዮርዳኖስ ትይዩ ራቅ ብለው ቆሙ። ኤልያስም ካባውን አውልቆ ጠቀለለውና ውሃውን መታበት፤ ከዚያም ውሃው ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ምድር ተሻገሩ። ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ኤልሳዕን፤ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ኤልሳዕም፣ “መንፈስህ በዕጥፍ እንዲያድርብኝ እለምንሃለሁ” ብሎ መለሰ። ኤልያስም፣ “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንም” አለው። እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ።
2 ነገሥት 2:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ፤ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ጒዞ ጀመሩ፤ በመንገድም ሳሉ ኤልያስ ኤልሳዕን “እነሆ፥ አንተ በዚህ ቈይ፤ እኔ ወደ ቤትኤል እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ከቶ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ቤትኤል ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ!” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቈይ፤ እኔ ወደ ኢያሪኮ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቈይ፤ እኔ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ጒዞአቸውን ቀጠሉ። ከነቢያቱም ኀምሳው ተከትለዋቸው ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ ኤልያስና ኤልሳዕም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ቆሙ፤ ኀምሳውም ነቢያት ደግሞ ጥቂት ራቅ ብለው ቆመው ነበር፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስ ካባውን አውልቆ በመጠቅለል ውሃውን መታው፤ ውሃውም ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎላቸው ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ በዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን “እኔ ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን እንዳደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ኤልሳዕም “የአንተ ተተኪ እንድሆን የሚያስችል መንፈስ በእጥፍ ስጠኝ” ሲል መለሰለት። ኤልያስም “ያቀረብከው ጥያቄ ከባድ ነው፤ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወሰድ ብታየኝ ይህን የጠየቅኸውን ስጦታ መቀበል ትችላለህ፤ ባታየኝ ግን ልታገኘው አትችልም” ሲል መለሰለት። እየተነጋገሩ እርምጃቸውን ቀጠሉ፤ ከዚያም በኋላ የእሳት ፈረሶች የሚስቡአቸው የእሳት ሠረገሎች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ተወሰደ።
2 ነገሥት 2:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ በሚያወጣው ጊዜ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ሄዱ። ኤልያስም ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚሁ ቈይ” አለው። ኤልሳዕም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ሕያው ነፍስህንም አልለይህም” አለው። ወደ ቤቴልም ደረሱ። በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ መጥተው፥ “እግዚአብሔር ጌታህን ከአንተ ለይቶ ዛሬ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። እርሱም፥ “አዎን፥ ዐውቄአለሁ፤ ዝም በሉ” አላቸው። ኤልያስም ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና፥ በዚህ ቈይ” አለው። ኤልሳዕም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ሕያው ነፍስህንም አልለይህም” አለው። ወደ ኢያሪኮም ደረሱ፤ በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው፥ “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። እርሱም፥ “አዎን፥ ዐውቄአለሁ፤ ዝም በሉ” አላቸው። ኤልያስም ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቈይ” አለው። ኤልሳዕም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ሕያው ነፍስህንም አልለይህም” አለው፤ ሁለቱም ሄዱ። ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፤ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር። ኤልያስም መጠምጠሚያውን ወስዶ ጠቀለለው፤ የዮርዳኖስንም ውኃ መታበት፤ ውኃውም ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ። ወጥተውም በምድረ በዳው ቆሙ። ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን” አለው፤ ኤልሳዕም፥ “መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ” አለ። ኤልያስም፥ “አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም” አለው። ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሄዱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በሁለቱ መካከል ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ንውጽውጽታ ወደ ሰማይ ወጣ።
2 ነገሥት 2:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ፥ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ። ኤልያስም ኤልሳዕን “እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ፤” አለው። ኤልሳዕም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም፤” አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ። በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን?” አሉት። እርሱም “አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፤” አላቸው። ኤልያስም “ኤልሳዕ ሆይ! እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፤” አለው። እርሱም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም” አለ። ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን?” አሉት። እርሱም “አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፤” ብሎ መለሰ። ኤልያስም “እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፤” አለው። እርሱም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም፤” አለ። ሁለቱም ሄዱ። ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፤ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር። ኤልያስም መጎናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፤ ውሃውንም መታ፤ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ። ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን “ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን፤” አለው፤ ኤልሳዕም “መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለ። እርሱም “አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም፤” አለ። ሲሄዱም፥ እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።
2 ነገሥት 2:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ፤ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ጉዞ ጀመሩ፤ በመንገድም ሳሉ ኤልያስ ኤልሳዕን “እነሆ፥ አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ቤትኤል እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ከቶ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ቤትኤል ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ!” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ኢያሪኮ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ጉዞአቸውን ቀጠሉ። ከነቢያቱም ኀምሳው ተከትለዋቸው ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ ኤልያስና ኤልሳዕም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ቆሙ፤ ኀምሳውም ነቢያት ደግሞ ጥቂት ራቅ ብለው ቆመው ነበር፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስ ካባውን አውልቆ በመጠቅለል ውሃውን መታው፤ ውሃውም ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎላቸው ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ በዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን “እኔ ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን እንዳደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ኤልሳዕም “የአንተ ተተኪ እንድሆን የሚያስችል መንፈስ በእጥፍ ስጠኝ” ሲል መለሰለት። ኤልያስም “ያቀረብከው ጥያቄ ከባድ ነው፤ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወሰድ ብታየኝ ይህን የጠየቅኸውን ስጦታ መቀበል ትችላለህ፤ ባታየኝ ግን ልታገኘው አትችልም” ሲል መለሰለት። እየተነጋገሩ እርምጃቸውን ቀጠሉ፤ ከዚያም በኋላ የእሳት ፈረሶች የሚስቡአቸው የእሳት ሠረገሎች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ተወሰደ።