የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 2

2
ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገ
1እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ፥ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ። 2ኤልያስም ኤልሳዕን “እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ፤” አለው። ኤልሳዕም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም፤” አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ። 3በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን?” አሉት። እርሱም “አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፤” አላቸው። 4ኤልያስም “ኤልሳዕ ሆይ! እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፤” አለው። እርሱም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም” አለ። ወደ ኢያሪኮም መጡ። 5በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን?” አሉት። እርሱም “አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ፤” ብሎ መለሰ። 6ኤልያስም “እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ፤” አለው። እርሱም “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ አልለይህም፤” አለ። ሁለቱም ሄዱ።
7ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፤ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር። 8ኤልያስም መጎናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፤ ውሃውንም መታ፤ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ። 9ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን “ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን፤” አለው፤ ኤልሳዕም “መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለ። 10እርሱም “አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም፤” አለ። 11ሲሄዱም፥ እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።
12ኤልሳዕም አይቶ፥ “አባቴ አባቴ ሆይ! የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞች!” ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።
ኤልሳዕ በኤልያስ እግር እንደተተካ
13ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ አነሣ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ። 14ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውሃውን መታና፥ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ፤ ውሃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ።
15ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል፤” አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፋ። 16እነርሱም “እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኀያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን፤” አሉት። እርሱም “አትስደዱ” አላቸው። 17እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ “ስደዱ” አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም። 18በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም “አትሂዱ አላልኋችሁምን?” አላቸው።
ኤልሳዕ ያደረጋቸው ተአምራት
19የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን “እነሆ፥ ጌታችን እንደምታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው፤ ውሃው ግን ክፉ ነው፤ ምድሪቱም ፍሬዋን ትጨነግፋለች፤” አሉት። 20እርሱም “አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፤ ጨውም ጨምሩበት፤” አለ፤ ያንንም አመጡለት። 21ውሃውም ወዳለበት ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ይህን ውሃ ፈውሼዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም፤’” አለ። 22ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ነገር ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሶአል።
23ከዚያም ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው “አንተ መላጣ፥ ውጣ! አንተ መላጣ፥ ውጣ!” ብለው አፌዙበት። 24ዘወርም ብሎ አያቸው፤ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው። 25ከዚያም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፤ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ