2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 2
2
ኤልያስ ወደ ሰማይ መነጠቁ
1እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ፤ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ጉዞ ጀመሩ፤ 2በመንገድም ሳሉ ኤልያስ ኤልሳዕን “እነሆ፥ አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ቤትኤል እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው።
ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ከቶ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ቤትኤል ሄዱ።
3በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት።
ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ!” ሲል መለሰላቸው።
4ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ኢያሪኮ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው።
ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ።
5በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት።
ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰላቸው።
6ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው።
ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ጉዞአቸውን ቀጠሉ። 7ከነቢያቱም ኀምሳው ተከትለዋቸው ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ ኤልያስና ኤልሳዕም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ቆሙ፤ ኀምሳውም ነቢያት ደግሞ ጥቂት ራቅ ብለው ቆመው ነበር፤ 8ከዚህ በኋላ ኤልያስ ካባውን አውልቆ በመጠቅለል ውሃውን መታው፤ ውሃውም ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎላቸው ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ 9#ዘዳ. 21፥17።በዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን “እኔ ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን እንዳደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው።
ኤልሳዕም “የአንተ ተተኪ እንድሆን የሚያስችል መንፈስ በእጥፍ ስጠኝ” ሲል መለሰለት።
10ኤልያስም “ያቀረብከው ጥያቄ ከባድ ነው፤ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወሰድ ብታየኝ ይህን የጠየቅኸውን ስጦታ መቀበል ትችላለህ፤ ባታየኝ ግን ልታገኘው አትችልም” ሲል መለሰለት።
11እየተነጋገሩ እርምጃቸውን ቀጠሉ፤ ከዚያም በኋላ የእሳት ፈረሶች የሚስቡአቸው የእሳት ሠረገሎች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ተወሰደ። 12#2ነገ. 13፥14፤ ሲራ. 48፥9፤12።ኤልሳዕም ይህን ሁሉ እያየ “የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች የሆንክ አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ!” እያለ ወደ ኤልያስ ጮኸ፤ ከዚያም በኋላ ኤልያስን ዳግመኛ አላየውም።
ኤልሳዕም ከኀዘን ብዛት የተነሣ ልብሱን ከሁለት ቀደደ፤ 13ከኤልያስም የወደቀውን ካባ ከመሬት አነሣ፤ ከዚያም ሄዶ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ቆመ። 14ውሃውንም በኤልያስ ካባ መትቶ፥ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ፤ ከዚያም በኋላ እንደገና በመታው ጊዜ ውሃው ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎለት ወደ ማዶ ተሻገረ፤ 15ከኢያሪኮ የመጡት ነቢያት እርሱን ባዩት ጊዜ “በኤልያስ ላይ ዐድሮ የነበረው የመንፈስ ኃይል በኤልሳዕ ላይ አርፏል!” አሉ፤ ወደ እርሱም በመቅረብ ጐንበስ ብለው እጅ ነሡት 16“እነሆ! በዚህ ጠንካሮች የሆንን ኀምሳ ሰዎች አለን፤ እንሂድና ጌታህን እንፈልገው፤ ምናልባት የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወስዶ በአንድ ተራራ ላይ ወይም ሸለቆ ውስጥ አሳርፎት ይሆናል።”
ኤልሳዕም “አትላኩአቸው” ሲል መለሰ።
17እነርሱ ግን እምቢ ለማለት እስኪያሳፍረው ድረስ አጥብቀው ስለ ለመኑት በጉዳዩ ተስማማና ኀምሳ ሰዎች ሄደው ሦስት ቀን ሙሉ ኤልያስን ፈለጉት፤ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም፤ 18ከዚያም በኋላ በኢያሪኮ ሆኖ ወደሚጠብቃቸው ወደ ኤልሳዕ ተመለሱ፤ ኤልሳዕም “እኔ ቀድሞውንስ አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?” አላቸው።
ኤልሳዕ ያደረጋቸው ተአምራት
19ጥቂት ሰዎች ከኢያሪኮ ወደ ኤልሳዕ መጥተው “ጌታችን አንተ እንደምታውቀው ይህች ምድር መልካም ናት፤ ውሃው ግን መጥፎ በመሆኑ ምድሪቱ ምርት አትሰጥም” አሉት።
20ኤልሳዕም “በአዲስ አፍላል ማሰሮ ውስጥ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” ብሎ አዘዘ። እነርሱም እንዳዘዛቸው አድርገው አመጡለት። 21እርሱም ወደ ምንጩ ሄዶ ጨውን በውሃው ውስጥ በመጨመር፥ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ‘እኔ ይህን ውሃ በመፈወስ ንጹሕ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ የሞትና የምርት አልባነት ምክንያት አይሆንም’” ሲል ተናገረ፤ 22ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤልሳዕ በተናገረው መሠረት ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ ንጹሕ ነው።
23ኤልሳዕም ወደ ቤትኤል ለመሄድ ከኢያሪኮ ተነሣ፤ በመንገድ ሳለ ከከተማይቱ በርከት ያሉ ልጆች ወጥተው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ “አንተ ራሰ መላጣ ከዚህ ውጣ!” እያሉ ጮኹበት።
24ኤልሳዕም መለስ ብሎ ዙሪያውን በመቃኘት፥ አተኲሮ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ በዚህም ጊዜ ሁለት እንስት ድቦች ከጫካ ወጥተው ከእነዚያ ልጆች መካከል አርባ ሁለቱን ሰባብረው ጣሉአቸው።
25ኤልሳዕም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ ዘግየት ብሎ ግን ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ