2 ነገሥት 17:24-41
2 ነገሥት 17:24-41 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ፥ ከአዋና ከሐማት፥ ከሴፌርዋይም ሰዎችን አመጣ፤ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶችን ሰደደባቸው፤ ይገድሉአቸውም ነበር። ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ፥ “ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው ሕዝቦች የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁም፤ የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፤ እነሆም፥ እየገደሉአቸው ነው” ብለው ተናገሩት። የአሦርም ንጉሥ፥ “ከዚያ ካመጣኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፤ የሀገሩንም አምላክ ሕግ ያስተምራቸው” ብሎ አዘዘ። ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱን ወስደው በቤቴል አኖሩት፤ ያም ካህን እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚፈሩት ያስተምራቸው ነበር። በየሕዝባቸውም አምላኮቻቸውን አደረጉ፤ ሳምራውያንም በሠሯቸው በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩባቸው ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። የባቢሎንም ሰዎች ሴኬቤቴናሆምን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌትን ሠሩ፤ የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፌርዋይም ሰዎች ለሴፌርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአኔሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ይሠዉ ነበር። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በሚኖሩበት ከተማ በሰማርያ በሠሩት በከፍታው ቦታ ጣዖቶቻቸውን አኖሩ። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናትን አደረጉ፤ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ እንደ ልማዳቸው ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ይፈራሉ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ያደርጋሉ። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ሌሎችን አማልክት አትፍሩአቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ አታምልኩአቸውም፤ አትሠዉላቸውም። ነገር ግን በታላቅ ኀይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን እርሱን ፍሩ፤ ለእርሱም ስገዱ፤ ለእርሱም ሠዉ። የጻፈላችሁንም ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ለዘለዓለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። ከእናንተም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻቸሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። ነገር ግን እነርሱ እንደሚያደርጉት ልማዳቸውን አትስሙ። እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም፥ የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲሁ ያደርጋሉ።”
2 ነገሥት 17:24-41 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የአሦርም ንጉሥ ሕዝቡን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋና ከሐማት፣ ከሴፈርዋይም ከተሞች አምጥቶ በእስራኤላውያን ቦታ እንዲገቡ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነርሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ ይኖሩ ጀመር። በዚያ መኖር እንደ ጀመሩም እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አንበሶች ሰደደባቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን ሰብረው ገደሉ። ለአሦርም ንጉሥ፣ “ወደ ሰማርያ ከተሞች ወስደህ ያሰፈርኸው ሕዝብ የዚያ አገር አምላክ የሚፈልገውን አላወቀም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰብሮ የሚገድል አንበሳ ላከበት” የሚል ወሬ ደረሰው። ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ “ከሰማርያ ማርካችሁ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን፣ በዚያው እንዲኖር መልሳችሁ ውሰዱትና የአገሩ አምላክ ምን እንደሚፈልግ ሕዝቡን ያስተምር” ሲል አዘዘ። ስለዚህ ከሰማርያ ማርከው ከወሰዷቸው ካህናት አንዱ ወደ ቤቴል ተመልሶ እግዚአብሔርን እንዴት መፍራት እንደሚገባቸው አስተማራቸው። ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ወገን በየሰፈረበት ከተማ የራሱን አምላክ ሠራ፤ ያንም ቀድሞ የሰማርያ ሕዝብ በኰረብታው ላይ በሠራው ማምለኪያ እየወሰደ አቆመ። ከባቢሎን የመጡት ሱኮት በኖትን፣ ከኩታ የመጡት ኔርጋልን፣ ከሐማት የመጡት አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅ የተባሉትን አማልክት ሲሠሩ፣ ከሴፈርዋይም የመጡት ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት አማልክታቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ወገን የመጣበትን ሕዝብ ልማድ ተከትሎ፣ በየኰረብታው ባሉት ቤተ ጣዖታት የሚያገለግሉትን ካህናት ሾመ። በአንድ በኩል እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፣ በሌላ በኩል ግን እንደየአገራቸው ልማድ የየራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር። ይህንም ልማዳቸውን እስከ ዛሬ ድረስ አልተዉትም፤ እግዚአብሔርን በአግባቡ አያመልኩም፤ እንዲሁም እስራኤል ብሎ ለጠራው ለያዕቆብ ዘሮች የሰጣቸውን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞችን አይከተሉም። እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋራ ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዝዟቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት አትፍሯቸው፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠዉላቸውም፤ መፍራት የሚገባችሁ ግን በታላቅ ኀይልና በተዘረጋች ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። ለርሱ ስገዱ፤ ለርሱም መሥዋዕት አቅርቡ። የጻፈላችሁን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞች ምን ጊዜም ተግታችሁ ጠብቁ። ሌሎች አማልክትን አታምልኩ። ከእናንተ ጋራ የገባሁትን ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትም አታምልኩ። ይልቅስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ የሚታደጋችሁ እርሱ ነውና።” ነገር ግን በቀደመው ልማዳቸው ጸኑ እንጂ አልተመለሱም። እነዚህ ሕዝቦች ምንም እንኳ በአንድ ወገን እግዚአብሔርን ቢያመልኩትም፣ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንም ያገለግሉ ነበር። ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው ያደረጉትን ዛሬም እንደ ቀጠሉበት ነው።
2 ነገሥት 17:24-41 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፤ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፤ ይገድሉአቸውም ነበር። ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ “ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፤ እነሆም፥ ገደሉአቸው፤” ብለው ተናገሩት። የአሦርም ንጉሥ “ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፤ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው፤ ብሎ አዘዘ። ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር። በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፤ ሳምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። የባቢሎንም ሰዎች ሱኮትበኖትን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌልን ሠሩ፤ የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፈርዋይም ሰዎችም ለሴፈርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአነሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፤ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር። እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው “ሌሎች አማልክትን አትፍሩ፤ አትስገዱላቸው፤ አታምልኩአቸው፤ አትሠዉላቸው፤ ነገር ግን በታላቅ ኀይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን እርሱን ፍሩ፤ ለእርሱም ስገዱ፤ ለእርሱም ሠዉ፤ የጻፈላችሁንም ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ለዘላለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። ነገር ግን እንደ ቀደመው ልማዳቸው አደረጉ እንጂ አልሰሙም። እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እንዲሁ እስከ ዛሬ ድረስ ያደርጋሉ።
2 ነገሥት 17:24-41 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን፥ ኩታ፥ ዓዋ፥ ሐማትና ሰፋርዋይም ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ። እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፤ ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት “በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብሮ የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው” የሚል ወሬ ደረሰው። ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ “ማርከን ካመጣናቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያም ተመልሶ በመሄድ የዚያችን አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ” ሲል አዘዘ። ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤትኤል ተቀመጠ፤ በዚያም ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባው አስተማረው። በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ። በዚህም ዐይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኔርጋል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፥ ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ ኢሺማ ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፤ ጣዖት ሠሩ፤ የዓዋ ሕዝብ ኒብሐዝና ታርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክታቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሰፋርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር። ከእያንዳንዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክታቸው ይሰግዱ ነበር። ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን አያመልኩም፤ ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶች፥ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፤ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፤ በታላቅ ኀይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፤ ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን፥ ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፤ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፤ እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፤ እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከጠላቶቻችሁ እጅ በመታደግ አድናችኋለሁ።” ነገር ግን እነዚያ አሕዛብ ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ። እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዐይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዐይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው።
2 ነገሥት 17:24-41 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን፥ ኩታ፥ ዓዋ፥ ሐማትና ሰፋርዋይም ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ። እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፤ ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት “በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብሮ የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው” የሚል ወሬ ደረሰው። ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ “ማርከን ካመጣናቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያም ተመልሶ በመሄድ የዚያችን አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ” ሲል አዘዘ። ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤትኤል ተቀመጠ፤ በዚያም ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባው አስተማረው። በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ። በዚህም ዓይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኔርጋል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፥ ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ ኢሺማ ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፤ ጣዖት ሠሩ፤ የዓዋ ሕዝብ ኒብሐዝና ታርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክታቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሰፋርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር። ከእያንዳንዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፤ በዚህም ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክታቸው ይሰግዱ ነበር። ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን አያመልኩም፤ ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶች፥ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፤ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፤ በታላቅ ኃይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፤ ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን፥ ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፤ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፤ እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፤ እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከጠላቶቻችሁ እጅ በመታደግ አድናችኋለሁ።” ነገር ግን እነዚያ አሕዛብ ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ። እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዓይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው።