የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 17

17
የእስራኤል ንጉሥ ሆሴዕ
1አካዝ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ 2እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ይሁን እንጂ የእርሱ በደል ከእርሱ በፊት የነበሩት የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙትን ያኽል አልነበረም፤ 3የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር ጦርነት በገጠመው ጊዜ ተሸንፎ እጁን በመስጠት በየዓመቱ ይገብርለት ጀመረ። 4ነገር ግን ከጥቂት ዓመቶች በኋላ ንጉሥ ሆሴዕ፥ ሶእ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ግብጽ ንጉሥ መልእክተኞች በመላክ ይረዳው ዘንድ ጠየቀ፤ በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ይሰጠው የነበረውንም ግብር አቆመ፤ ሰልምናሶር ይህን በሰማ ጊዜ ሆሴዕን አስይዞ ወህኒ ቤት አስገባው።
የሰማርያ መውደቅ
5ከዚህ በኋላ ሰልምናሶር አገሪቱን ወረረና ሰማርያን ለሦስት ዓመት ከበባት፤ 6ይኸውም ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ሰልምናሶር ድል አድርጎ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም ማርኮ በእስረኛነት ወደ አሦር ወሰዳቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ፥ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ ውስጥ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ እንዲሁም ሌሎቹ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ።
7ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን በሠሩት ኃጢአት ከግብጽ ንጉሥ እጅ በመታደግ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በማሳዘናቸው ነበር፤ ይኸውም ለባዕዳን አማልክት ሰገዱ፤ 8ሕዝቡ ወደ ፊት እየገፋ በመጣ ጊዜ ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸውን የአሕዛብን መጥፎ ልማድ ተከተሉ፤ እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት ያሠራጩትን መጥፎ ልማድ ተቀባዮች ሆኑ። 9እስራኤላውያን አምላካቸው እግዚአብሔር የሚጠላውን ነገር ሁሉ አደረጉ፤ ከዘብ ጠባቂዎች ማማ አንሥቶ እስከ ትልቅ ከተማ ድረስ በገጠር ከተሞቻቸው ሁሉ በየኰረብታዎቹ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፤ 10#1ነገ. 14፥23።በኰረብቶች ሁሉ ላይና በየዛፉ ጥላ ሥር የድንጋይ ዐምዶችንና አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎች አቆሙ፤ 11እግዚአብሔር ከምድሪቱ ነቃቅሎ ያስወጣቸውን የአረማውያንን ሕዝብ ልማድ በመከተል በአሕዛብ መሠዊያዎች ሁሉ ላይ ዕጣን አጠኑ፤ በዚህም ክፉ ሥራቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ፤ 12እግዚአብሔር ለጣዖት እንዳይሰግዱ ያዘዛቸውንም ሕግ ሁሉ አፈረሱ።
13እግዚአብሔርም እስራኤልንና ይሁዳን የሚያስጠነቅቁ መልእክተኞችንና ነቢያትን በመላክ “ከክፉ መንገዳችሁ ሁሉ ተመለሱ፤ አገልጋዮቼ በሆኑት ነቢያትና ባለ ራእዮች አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተም በሰጠሁት ሕጎችና ትእዛዞች የተጻፈውን ሥርዓቴን ጠብቁ” ብሎ ነግሮአቸው ነበር። 14እነርሱ ግን መታዘዝ አልፈለጉም፤ በአምላካቸው በእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው እልኸኞች ሆኑ፤ 15የሰጣቸውንም ድንጋጌ አልተቀበሉም፤ ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ የሰጣቸውንም ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ ቸል አሉ፤ ለከንቱ ጣዖቶች በመስገድ ራሳቸውም ከንቱዎች ሆኑ፤ የእነርሱን መጥፎ ምሳሌነት እንዳይወርሱ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዝ በመሻር በዙሪያቸው የሚኖሩ የአሕዛብን ልማድ ሁሉ ተከተሉ። 16#1ነገ. 12፥28።የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ በመጣስ የሚሰግዱላቸውን ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጥጆችን አቆሙ፤ እንዲሁም አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሠሩ፤ ለከዋክብት ሰገዱ፤ በዓል ተብሎ ለሚጠራውም ባዕድ አምላክ አገልጋዮች ሆኑ። 17#ዘዳ. 18፥10።ለእነዚያም አሕዛብ አማልክት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፤ ከሙታን ጠሪዎችና ከጠንቋዮችም ምክር ጠየቁ፤ እግዚአብሔር ለሚጠላው ክፉ ነገር ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ። 18እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ተቆጥቶ የይሁዳን መንግሥት ብቻ በመተው እስራኤላውያንን ከፊቱ አስወገደ።
19ነገር ግን የይሁዳ ሰዎችም ቢሆኑ፥ አምላካቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዞች አልጠበቁም ነበር፤ እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ የተቀበሉትን ልማድ ተከታዮች ነበሩ። 20እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሁሉ ተዋቸው፤ ከፊቱም እስኪወገዱ ድረስ በዝባዦች ለሆኑት ጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው።
21እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከይሁዳ ከለየ በኋላ እስራኤላውያን የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን መርጠው አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን እንዲተው በማድረግ አሠቃቂ ወደ ሆነ ኃጢአት መራቸው፤ 22እስራኤላውያንም በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ጸኑ፤ ከዚያም አልተመለሱም። 23ጌታ በባርያዎቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት፥ ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በዚያው ቀጠሉበት፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ከሀገሩ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ፤ አሁንም በዚያው ይገኛል።
አሦራውያን በእስራኤል ምድር እንዲሰፍሩ መደረጉ
24የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን፥ ኩታ፥ ዓዋ፥ ሐማትና ሰፋርዋይም ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ። 25እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር። ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፤ 26ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት “በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብሮ የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው” የሚል ወሬ ደረሰው። 27ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ “ማርከን ካመጣናቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያም ተመልሶ በመሄድ የዚያችን አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ” ሲል አዘዘ። 28ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤትኤል ተቀመጠ፤ በዚያም ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባው አስተማረው።
29በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ። 30በዚህም ዓይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኔርጋል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፥ ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ ኢሺማ ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም፤ ጣዖት ሠሩ፤ 31የዓዋ ሕዝብ ኒብሐዝና ታርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክታቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሰፋርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 32እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር። ከእያንዳንዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፤ 33በዚህም ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክታቸው ይሰግዱ ነበር።
34 # ዘፍ. 32፥28፤ 35፥10። ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን አያመልኩም፤ ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶች፥ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም። 35#ዘፀ. 20፥5፤ ዘዳ. 5፥9።እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፤ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፤ 36#ዘዳ. 6፥13።በታላቅ ኃይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፤ 37ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን፥ ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፤ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፤ 38እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፤ 39እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከጠላቶቻችሁ እጅ በመታደግ አድናችኋለሁ።” 40ነገር ግን እነዚያ አሕዛብ ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ።
41እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዓይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ