የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 18

18
የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ
(2ዜ.መ. 29፥1-231፥1)
1የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 2በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሀያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሀያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱም አቢያ ተብላ የምትጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበረች፤ 3የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ። 4#ዘኍ. 21፥9።የአሕዛብን የማምለኪያ ስፍራዎችን ደመሰሰ፤ የድንጋይ ዐምዶችን ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የተቀረጹትን ምስሎች ሁሉ አንኮታክቶ ጣለ፤ ሙሴ ከነሐስ ሠርቶት የነበረውን ኔሑሽታን ተብሎ የሚጠራውን የእባብ ምስል ሰባብሮ አደቀቀ፤ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ግን እስራኤላውያን ለእርሱ ዕጣን ያጥኑለት ነበር። 5ሕዝቅያስ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ተማመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ ወዲህ እርሱን የመሰለ ሌላ ንጉሥ በይሁዳ አልተነሣም፤ 6ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ ከእርሱ መንገድ የራቀበት ጊዜ የለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽም ነበር። 7ስለዚህም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆኖ ስለሚረዳው የሚሠራው ሁሉ በተቃና ሁኔታ ይከናወንለት ነበር፤ ሕዝቅያስ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ላይ ዐምፆ ለእርሱ መገዛትን አሻፈረኝ አለ። 8ፍልስጥኤማውያንንም ድል ነሥቶ ከትንሽ መንደር እስከ ታላቅ ከተማ ጋዛንና በዙሪያው የሚገኘውን ግዛት ጭምር እነርሱ የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ ወረረ።
9ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ይህም ማለት ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፤ 10በተከበበችበትም በሦስተኛው ዓመት ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፥ ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። 11የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ ሌሎቹ ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ።
12ሰማርያ የወደቀችበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ በሆነው በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ቃሉን ማዳመጥም ሆነ ሕጉን መጠበቅ አልፈለጉም።
አሦራውያን በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል መዛታቸው
(2ዜ.መ. 32፥1-19ኢሳ. 36፥1-22)
13ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም አደጋ በመጣል የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ያዘ፤ 14ሕዝቅያስም በላኪሽ ሰፍሮ ለነበረው ለሰናክሬም “እኔ በድያለሁ፤ እባክህን አቁም፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ” ሲል መልእክት ላከ፤ ንጉሠ ነገሥቱም “እኔ የምፈልገው ዐሥር ሺህ ኪሎ ብርና አንድ ሺህ ኪሎ ወርቅ እንድትልክልኝ ነው” ሲል መለሰለት። 15ሕዝቅያስም በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረውን ብር ሁሉ ሰብስቦ ላከለት፤ 16እንዲሁም በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሮች ላይ ተለብጦ የነበረውን ወርቅና እርሱም ራሱ በቤተ መቅደሱ የበር ዐምዶች ላይ ለብጦት የነበረውን ወርቅ ጭምር ወደ ሰናክሬም ላከ። 17ይህ በዚህ እንዳለ የአሦር ንጉሠ ነገሥት እንደገና የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት ከላኪሽ ተንቀሳቅሶ ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት በሕዝቅያስ ላይ አደጋ እንዲጥልበት አዘዘ፤ ያም ሠራዊት ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ሦስት የጦር አዛዦቹ የሚመራ ነበር፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ ከላይኛው ኲሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አጠገብ ወደ ልብስ አጣቢዎች መስክ የሚወስደውን መንገድ ያዙ፤ 18ከዚያም በኋላ ወደ ሕዝቅያስ መልእክት ላኩበት፤ ሕዝቅያስም ባለሟሎቹ የሆኑ ሦስት ባለ ሥልጣኖች ሄደው እንዲገናኙአቸው አዘዘ፤ እነርሱም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነ የሒልቂያ ልጅ ኤልያቄም፥ እንዲሁም የቤተ መንግሥት ጸሐፊ የሆነው ሼብናና የቤተ መዛግብት ኃላፊ የሆነው የአሳፍ ልጅ ዮአሕ ነበሩ፤ 19ከአሦር የጦር አዛዦች አንዱ እንዲህ አላቸው፦ “ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ለመሆኑ እንደዚህ አድርገህ የተማመንክበት ነገር ምንድነው? 20የቃላት ጋጋታ የጦርነትን ስልትና ኃይል የሚተካ ይመስልሃልን? ማን ይረዳኛል ብለህ ነው በአሦር ላይ ለማመፅ ያሰብከው? 21የግብጽ ንጉሥ ይረዳኛል ብለህ አስበህ ከሆነ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ እንደሚመረኰዝ ሰው መሆንህ ነው፤ እርሱ ተሰብሮ ስንጣሪው እጅህን ያቆስልሃል፤ እንግዲህ የግብጽ ንጉሥ ለሚተማመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው’ ሲል የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይጠይቅሃል።”
22የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፦ “አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ አድርገህ ታስባለህን? ይህማ እንዳይሆን፥ አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ ‘የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው’ ብለህ ወስነሃል። 23አሁንም በንጉሠ ነገሥቱ ስም ለፍልሚያ እጠይቅሃለሁ፤ መጋለብ የሚችሉ በቂ ሰዎች ታገኝ እንደሆነ እስቲ ሁለት ሺህ ፈረሶች ልስጥህ! 24አንተ እኮ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ከአሦር ተራ የጦር መኰንን ጋር እንኳ መወዳደር አትችልም፤ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይልኩልኛል ብለህ የምትጠባበቀውም በዚሁ ምክንያት ነው። 25እኔ በአንተ አገር ላይ አደጋ የጣልኩባትና የደመሰስኳት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዞኛል።”
26ከዚህም በኋላ ኤልያቄምና፥ ሼብና እንዲሁም ዮአሕ ይህን የጦር አዛዥ “ፍቹን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጽር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን” አሉት።
27እርሱም “የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣችሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? ከቶ አይደለም፤ ልክ እንደ እናንተ ኩሳቸውን ለመብላትና ሽንታቸውን ለመጠጣት የሚገደዱ ሰዎችም ጭምር ስለ ሆኑ፥ እኔ የምናገረውን በቅጽሩ ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት ነው” ሲል መለሰላቸው።
28ከዚህም በኋላ ያ የአሦር ባለ ሥልጣን ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ፤ “የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሚነግራችሁን ስሙ! 29በሕዝቅያስ አትታለሉ! እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም! 30ሕዝቅያስ ‘በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ ያድናችኋል፤ ከተማችንም በአሦርያውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል’ እያለ የሚሰብካችሁን አትስሙ፤ 31ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከከተማችሁ ወጥታችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ አዞአችኋል፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁም እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላና የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጉድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ 32ይህም ሁሉ የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር ወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ምድሪቱም የወይራ ፍሬና የወይራ ዘይት እንዲሁም ማር የሞላባት ናት፤ ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዛችሁን ብትፈጽሙ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም፤ ስለዚህ ሕዝቅያስ ‘እግዚአብሔር ይታደጋችኋል’ እያለ በመስበክ አያሞኛችሁ፤ 33ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት አንዱ እንኳ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አገሩን ያዳነ ይገኛልን? 34ታዲያ ይህ ከሆነ የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዋይም የሄናዕና የዒዋ አማልክትስ የት ደረሱ? ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ማዳን ችሎአልን? 35የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ከንጉሠ ነገሥታቶቻችን እጅ አገሮቻቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እንግዲህ እናንተ ‘እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል’ ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?”
36ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ፤ 37ከዚህ በኋላ ኤልያቄምና ሼብና እንዲሁም ዮአሕ በኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቀርበው የአሦራውያን ባለ ሥልጣን የተናገረውን አስረዱት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ