የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 19

19
ንጉሥ ሕዝቅያስ የነቢዩን የኢሳይያስን ምክር መጠየቁ
(ኢሳ. 37፥1-7)
1ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በኀዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ፤ 2ወዲያውም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነውን ኤልያቄምን፥ የቤተ መንግሥቱን ጸሐፊ ሼብናንና ሽማግሌዎች ካህናትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ራሳቸው ማቅ ለብሰው ነበር፤ 3ለኢሳይያስም እንዲነግሩት የላከው መልእክት ከዚህ የሚከተለው ነው፦ “ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፤ 4የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባለሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢውን ይቀጣ ይሆናል፤ ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ለተረፉት ሰዎች እባክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።”
5የንጉሥ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፥ 6ኢሳይያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብላችሁ ለጌታችሁ ንገሩት አላቸው፤ ‘የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ሲሰድቡኝ ስለ ሰማችሁት ቃል አትፍሩአቸው። 7እነሆ፥ እኔ የሽብር ወሬ የሚያሰማ መንፈስ እልክበታለሁ፤ ስለዚህም ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲሄድና እዚያም በገዛ ምድሩ በሰይፍ ተመትቶ እንዲሞት አደርጋለሁ።’”
አሦራውያን ሌላ የዛቻ መልእክት መላካቸው
(ኢሳ. 37፥8-20)
8የአሦር የጦር አዛዥ፥ የአሦር ንጉሥ ከሰፈሩ ከላኪሽ ተነሥቶ ሊብናን ሊያጠቃ እንደ ሄደ በመስማቱ እርሱም ወደዚያው ሄደ። 9በኢትዮጵያ ንጉሥ በቲርሃቃ የሚመራ የግብጽ ሠራዊት እነርሱን ለመውጋት በመገሥገሥ ላይ መሆኑን አሦራውያን ሰሙ፤ ወዲያውኑ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ በመልእክተኞች እጅ ላከ፦ 10“የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሆይ፥ የምትታመንበት አምላክ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አትወድቅም’ ብሎ አያታልህ፤ 11የአሦር ነገሥታት አገሮችን ሁሉ እንዴት ፈጽመው እንደ ደመሰሱ ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 12የቀድሞ አባቶቼ የጎዛንን፥ የካራንና የሬጼፍን ከተሞች አጥፍተዋል፤ በተላሳር የሚኖሩትን የዔዳንን ሕዝብ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ከአማልክታቸው አንድ እንኳ ሊያድናቸው ችሎአልን? 13ለመሆኑ የሐማት፥ የአርፋድ፥ የሰፋርዋይም፥ የሄናዕና የዒዋ ከተሞች ነገሥታት የት አሉ?”
14ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልክተኞች ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ወስዶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው፤ 15#ዘፀ. 25፥22።እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ኪሩቤል ተብለው በሚጠሩ መላእክት ላይ የተቀመጥህ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ የዓለምንም መንግሥታት የምትመራ አንተ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህ አንተ ነህ፤ 16አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ የደረሰብንን ነገር ሁሉ ተመልከት፥ ሕያው አምላክን አንተን በመስደብ ሰናክሬም የተናገረውን የዛቻ ቃል ሁሉ አድምጥ፤ 17እግዚአብሔር ሆይ፥ የአሦር ነገሥታት ብዙ ሕዝቦችና ምድራቸውን መደምሰሳቸው እርግጥ ነው። 18ከእንጨትና ከድንጋይ ተጠርበው የተሠሩ የሰው እጅ ሥራ እንጂ አማልክት ስላልነበሩ በእሳት ላይ ጥለው አጠፉአቸው። 19እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን የዓለም መንግሥታት ሁሉ ያውቁ ዘንድ አሁን ከአሦር ንጉሥ በመታደግ አድነን።”
ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ያስተላለፈው መልእክት
(ኢሳ. 37፥21-38)
20ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ አሦር ንጉሠ ነገሥት ስለ ሰናክሬም ዛቻ ያቀረብከውን ጸሎት ሰምቻለሁ፤ 21ስለ እርሱ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ የጽዮን ድንግል ትንቅሃለች፤ ታፌዝብሃለች፤ አንተ እየሸሸህ ሳለህ፥ የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች ከኋላህ ሆነው ራሳቸውን ይነቀንቁብሃል። 22የሰደብከውና የተዳፈርከው ማንን ነው? ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው በማን ላይ ነው? በትዕቢትስ ዐይንህን ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ ነው። 23በመልክተኞችህ አማካይነት፥ በእግዚአብሔር ላይ ስድብህን ከምረሃል፤’ ‘በሠረገሎቼ ከፍተኛ ወደ ሆኑት ተራራዎች፤ ወደ ሊባኖስ ጫፍ ወጥቼአለሁ፤ ረጃጅሞቹን የሊባኖስ ዛፎችዋንና ምርጦች ዝግባ ቆርጬአለሁ፤ ወደ ዳርቻዋና ውብ ወደ ሆነው ጫካዋ ደርሼአለሁ፤’ ብለሃል። 24‘በባዕድ አገር ጉድጓድ ቆፍሬ፥ ውሃ ጠጣሁ፤ በእግሬ ኮቴዎች የግብጽን ወንዞች አድርቄአለሁ’ ብለህ ታብየሃል። 25ሰናክሬም ሆይ! አስተውል፤ ጥንቱኑ እኔ እንደ ወሰንኩት፥ በቀድሞ ዘመን እንደ ዐቀድኩትና አሁን በሥራ ላይ ባዋልኩት መሠረት የተጠናከሩ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት እንድትለውጥ ያደረግኹህ እኔ መሆኔን አልሰማህምን? 26የእነዚያ አገር ነዋሪዎች ኃይላቸው ተዳክሞ፥ ተስፋ በመቁረጥ እንዳያፍሩ ተደርገው በምሥራቅ ነፋስ እንደ ተመቱ፥ የመስክ አትክልቶች፥ እንደ ቀጨጩ አረንጓዴ ቡቃያዎች፥ በጣራ ላይ እንደ በቀለ ሣር ናቸው። 27እኔ ግን መነሣትህንና መቀመጥህን፥ መውጣትህንና መግባትህን፥ እንዲሁም እኔን መቃወምህን ዐውቃለሁ። 28በእኔ ላይ ያለው ተቃውሞህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ በአፍንጫህ ስናጋ፥ በአፍህ ልጓም አድርጌ፥ በመጣህበት መንገድ እመልስሃለሁ።”
29ከዚህ በኋላ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ምልክቱ ይህ ነው፥ በአሁኑና በሚቀጥለው ዓመት ሳይዘሩት የሚበቅለውንና የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን የራሳችሁን እህል ዘርታችሁ ታመርታላችሁ፤ ወይንም ተክላችሁ ፍሬውን ትበላላችሁ፤ 30በይሁዳ ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ወደ መሬት ሥር ሰድዶ እንደሚያድግና እንደሚያፈራ ተክል ይሆናሉ፤ 31ከኢየሩሳሌምና ከጽዮን ተራራ የተረፉት ወገኖች ይወጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ከመፈጸም አይመለስም።”
32እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን ንጉሠ ነገሥት የተናገረውም ቃል ይህ ነው፦ “ሰናክሬም ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባባትም፤ አንድ ፍላጻ እንኳ አይወረውርባትም፤ ጋሻ ያነገበ ወታደርም ወደ እርሷ አይቀርብም፤ በዐፈር ቁልልም አትከበብም። 33እርሱ ወደዚህች ከተማ ሳይገባ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ 34ስለ ራሴ ክብር እንዲሁም ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ይህችን ከተማ እኔ ራሴ ተከላክዬ አድናታለሁ።”
35በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አሦራውያን ሰፈር አልፎ አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ በማግስቱ በማለዳ ሰዎች በሚነቁበት ጊዜ ሁሉም ሞተው ተገኙ። 36ከዚህ በኋላ የአሦራውያን ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም ወደ ኋላው በማፈግፈግ ወደ ነነዌ ተመለሰ። 37ከዕለታት በአንዱ ቀን ኒስሮክ በሚል ስም በሚጠራው ባዕድ አምላኩ ቤተ መቅደስ ውስጥ በስግደት ላይ እንዳለ፥ ከልጆቹ ሁለቱ በተለይ አድራሜሌክና ሣሬጼር ተብለው የሚጠሩት በሰይፍ ገደሉት፤ እነርሱም ወደ አራራት አምልጠው ሄዱ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ከልጆቹ አንዱ አስራዶ የተባለው ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ