2 ቆሮንቶስ 10:7-18
2 ቆሮንቶስ 10:7-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም የክርስቶስ በመሆኑ ቢመካ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን ሊገነዘብ ይገባዋል። ጌታ በሰጠን ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበልነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና። በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። አንዳንዶች፣ “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነቱ ሲታይ ደካማ፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይላሉ። እንዲህ የሚሉ ሰዎች በሩቅ ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን ሁሉ በቅርብ ሆነን በተግባራችን የምንገልጸውም እንደዚያው መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ሰዎች ጋራ ራሳችንን ልንመድብ ወይም ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውን በራሳቸው ሲመዝኑና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋራ ሲያነጻጽሩ አስተዋዮች አይደሉም። እኛ ግን ከመጠን በላይ አንመካም፤ የምንመካው እግዚአብሔር በመደበልንና እስከ እናንተም እንኳ በሚደርሰው የአገልግሎታችን ወሰን ነው። የክርስቶስን ወንጌል ይዘን ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ፣ ከተመደበልን የአገልግሎት ወሰን አላለፍንም። ደግሞም ሌሎች በደከሙበት ሥራ ከመጠን በላይ በመመካት ከተመደበልን ወሰን አናልፍም፤ ይልቁንም እምነታችሁ እያደገ በሄደ ቍጥር በእናንተ ዘንድ የተመደበልን አገልግሎት እየሰፋ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን። ስለዚህ በሌላው ሰው ክልል አስቀድሞ በተሠራ ሥራ ሳንመካ፣ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር ወንጌልን መስበክ እንችላለን። ነገር ግን፣ “የሚመካ በጌታ ይመካ”፤ ምክንያቱም ጌታ ራሱ የሚያመሰግነው እንጂ፣ ራሱን በራሱ የሚያመሰግን ተቀባይነት አይኖረውም።
2 ቆሮንቶስ 10:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቁጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛ ደግሞ እንዲሁ ነን። ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም። በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ። መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን። ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና።
2 ቆሮንቶስ 10:7-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እናንተ የምትመለከቱት በውጪ የሚታየውን ነገር ብቻ ነው፤ ማንም ሰው የክርስቶስ ነኝ ብሎ ቢተማመን እንደገና ያስብበት፤ እኛም እንደ እርሱ የክርስቶስ መሆናችንን ይገንዘብ። ጌታ ስለ ሰጠን ሥልጣን በጣም ብመካም አላፍርበትም፤ ይህ ሥልጣን የተሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም። በመልእክቴ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። ምናልባት አንዳንዶች “የጳውሎስ መልእክቶች ከባዶችና ብርቱዎች ናቸው፤ እርሱ ራሱ ከእኛ ጋር ሲሆን ግን ደካማ ነው፤ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይሉ ይሆናል። ይህን የሚሉ ሰዎች እኛ በሩቅ ሆነን በመልእክቶቻችን በምንጽፈውና በቅርብም ከእናንተ ጋር ሆነን በምንሠራው መካከል ምንም ልዩነት አለመኖሩን ይገንዘቡ። ይሁን እንጂ ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ራሳችንን ልናወዳድር ወይም ራሳችንን ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ግን ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር በማመዛዘናቸውና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር በማወዳደራቸው አስተዋዮች አይደሉም። እኛ ግን እስከ እናንተም እንኳ እስክንደርስ እግዚአብሔር በሰጠን የሥራ ክልል እንመካለን እንጂ ከመጠን በላይ የምንመካ አይደለንም። እናንተም ያላችሁት በሥራችን ክልል ውስጥ ስለ ሆነ የክርስቶስን ወንጌል ለማስተማር ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ ከዚያ ክልል አላለፍንም። ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ከወሰነልን ክልል አልፈን በሌሎች ሥራ ያለ ልክ አንመካም፤ ይልቅስ እምነታችሁ እንዲያድግና የእኛም ሥራ እግዚአብሔር በወሰነልን ክልል በእናንተ መካከል ይበልጥ እንዲስፋፋ ተስፋ እናደርጋለን። እንግዲህ በሌላው ሰው የሥራ ክልል ውስጥ ገብተን አስቀድሞ በተሠራው ሥራ ሳንመካ ከእናንተ ወዲያ ባሉት አገሮች የምሥራቹን ቃል ለማብሠር እንችላለን። ነገር ግን “የሚመካ በጌታ ይመካ።” ሰው ለመመስገን የሚበቃው ጌታ ሲያመሰግነው ነው እንጂ ራሱን በራሱ ሲያመሰግን አይደለም።
2 ቆሮንቶስ 10:7-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ፤ ማንም በክርስቶስ ያመነ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቍጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛም እንዲሁ ነንና። እናንተን ለማነጽ እንጂ፥ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ በሰጠን ሥልጣን እጅግ የተመካሁት መመካት ቢኖር አላፍርም። ነገር ግን በመልእክቶች የማስፈራራችሁ እንዳይመስላችሁ፥ ይህን ትምክሕቴን እተወዋለሁ። ከሰዎች መካከል “መልእክቶቹ ከባዶችና አስጨናቂዎች ናቸው፤ ሰውነቱ ግን ደካማ ነው፤ ነገሩም ተርታ ነው” የሚሉ አሉና። ነገር ግን ይህን ነገር የሚናገር ይህን ይወቅ፤ በሌለንበት ጊዜ በመልእክታችን እንደ ተገለጠው እንደ ቃላችን፥ ባለንበትም ጊዜ በሥራችን እንዲሁ ነን። እነርሱ ራሳቸውን በአሰቡትና በገመገሙት መጠን ራሳቸውን ከሚያመሰግኑት ሰዎች ጋር ራሳችንን ልንቈጥር፥ ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውም የሚናገሩትን ትርጕሙን አያውቁትም። እኛስ ወደ እናንተ እስክንደርስ ድረስ እግዚአብሔር በወሰነልን ሕግና ሥርዐት እንጂ፥ ከዐቅማችን አልፈን እጅግ አንመካም። ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን፥ ራሳችንን የምናመሰግን አይደለምና፤ ነገር ግን የክርስቶስን ሕግ በማስተማር ወደ እናንተ ደርሰናል። እኛስ በማይገባ ሌላ በደከመበት አንመካም፤ ነገር ግን ሃይማኖታችሁ እንድትሰፋ፥ የተሠራችላችሁ ሕግም በእናንተ እንድትጸና ተስፋ እናደርጋለን። አብዝተንም እናስተምራችኋለን፤ ያንጊዜም መጠናችን ከሥራችን ጋር ከፍ ከፍ ይላል፤ እኛስ ቀና ባልሆነውና በማይገባው አንመካም። “የሚመካ ግን በእግዚአብሔር ይመካ።” እግዚአብሔር ያከበረው ብቻ ይከብራል እንጂ ራሱን የሚያከብር የተመረጠ አይደለም።
2 ቆሮንቶስ 10:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ከሆነ፥ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን እንዳይዘነጋ። በሥልጣናችን ከበፊቱ ይልቅ አሁን ብመካም እንኳን፥ ይህን ጌታ የሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ስላልሆነ አላፍርበትም። በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ እንዳይመስላችሁ። አንዳንዶች “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ሰውነቱ ሲታይ ግን ደካማ ነው፤ ንግግሩም የተናቀ ነው፤” ይላሉ። እንዲህ የሚሉን፥ በርቀት ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን በአካልም ስንገኝ የምናደርገው መሆኑን፥ ይወቁት። ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን መቁጠር ወይም ራሳችንን ማስተያየት አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ እርስ በራሳቸው ሲያመዛዝኑ፥ እርስ በራሳቸውም ሲተያዩ፥ አስተዋይ አይደሉም። እኛ ግን፥ እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን፥ እስከ እናንተ በሚደርስ ወሰን እንጂ፥ ያለ ልክ አንመካም። ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፤ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ ድረስ መጥተናል፥ እናንተን በማካለል እንዳለፍናችሁ በማሰብ ወሰን አናልፍም። በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፤ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ፥ የምንሠራበት ወሰን እየሰፋ ይሄዳል፤ በሌላው ክፍል ስለ ተሠራው ነገር መመካት ሳያስፈልገን፥ ከእናንተ አልፎ ባለው አገር ወንጌልን ለማብሰር ያስችለናል። “የሚመካ በጌታ ይመካ፤” ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ፥ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለም።