የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10:7-18

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10:7-18 አማ05

እናንተ የምትመለከቱት በውጪ የሚታየውን ነገር ብቻ ነው፤ ማንም ሰው የክርስቶስ ነኝ ብሎ ቢተማመን እንደገና ያስብበት፤ እኛም እንደ እርሱ የክርስቶስ መሆናችንን ይገንዘብ። ጌታ ስለ ሰጠን ሥልጣን በጣም ብመካም አላፍርበትም፤ ይህ ሥልጣን የተሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም። በመልእክቴ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። ምናልባት አንዳንዶች “የጳውሎስ መልእክቶች ከባዶችና ብርቱዎች ናቸው፤ እርሱ ራሱ ከእኛ ጋር ሲሆን ግን ደካማ ነው፤ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይሉ ይሆናል። ይህን የሚሉ ሰዎች እኛ በሩቅ ሆነን በመልእክቶቻችን በምንጽፈውና በቅርብም ከእናንተ ጋር ሆነን በምንሠራው መካከል ምንም ልዩነት አለመኖሩን ይገንዘቡ። ይሁን እንጂ ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ራሳችንን ልናወዳድር ወይም ራሳችንን ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ግን ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር በማመዛዘናቸውና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር በማወዳደራቸው አስተዋዮች አይደሉም። እኛ ግን እስከ እናንተም እንኳ እስክንደርስ እግዚአብሔር በሰጠን የሥራ ክልል እንመካለን እንጂ ከመጠን በላይ የምንመካ አይደለንም። እናንተም ያላችሁት በሥራችን ክልል ውስጥ ስለ ሆነ የክርስቶስን ወንጌል ለማስተማር ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ ከዚያ ክልል አላለፍንም። ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ከወሰነልን ክልል አልፈን በሌሎች ሥራ ያለ ልክ አንመካም፤ ይልቅስ እምነታችሁ እንዲያድግና የእኛም ሥራ እግዚአብሔር በወሰነልን ክልል በእናንተ መካከል ይበልጥ እንዲስፋፋ ተስፋ እናደርጋለን። እንግዲህ በሌላው ሰው የሥራ ክልል ውስጥ ገብተን አስቀድሞ በተሠራው ሥራ ሳንመካ ከእናንተ ወዲያ ባሉት አገሮች የምሥራቹን ቃል ለማብሠር እንችላለን። ነገር ግን “የሚመካ በጌታ ይመካ።” ሰው ለመመስገን የሚበቃው ጌታ ሲያመሰግነው ነው እንጂ ራሱን በራሱ ሲያመሰግን አይደለም።