የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10:7-18

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10:7-18 መቅካእኤ

በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ከሆነ፥ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን እንዳይዘነጋ። በሥልጣናችን ከበፊቱ ይልቅ አሁን ብመካም እንኳን፥ ይህን ጌታ የሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ስላልሆነ አላፍርበትም። በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ እንዳይመስላችሁ። አንዳንዶች “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ሰውነቱ ሲታይ ግን ደካማ ነው፤ ንግግሩም የተናቀ ነው፤” ይላሉ። እንዲህ የሚሉን፥ በርቀት ሆነን በመልእክታችን የምንናገረውን በአካልም ስንገኝ የምናደርገው መሆኑን፥ ይወቁት። ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን መቁጠር ወይም ራሳችንን ማስተያየት አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ እርስ በራሳቸው ሲያመዛዝኑ፥ እርስ በራሳቸውም ሲተያዩ፥ አስተዋይ አይደሉም። እኛ ግን፥ እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን፥ እስከ እናንተ በሚደርስ ወሰን እንጂ፥ ያለ ልክ አንመካም። ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፤ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ ድረስ መጥተናል፥ እናንተን በማካለል እንዳለፍናችሁ በማሰብ ወሰን አናልፍም። በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፤ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ፥ የምንሠራበት ወሰን እየሰፋ ይሄዳል፤ በሌላው ክፍል ስለ ተሠራው ነገር መመካት ሳያስፈልገን፥ ከእናንተ አልፎ ባለው አገር ወንጌልን ለማብሰር ያስችለናል። “የሚመካ በጌታ ይመካ፤” ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ፥ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለም።