2 ቆሮንቶስ 1:8-14
2 ቆሮንቶስ 1:8-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወድዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው። እርሱ እንዲህ ካለው የሞት አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ወደ ፊትም ደግሞ እንደሚያድነን ተስፋችንን በርሱ ላይ ጥለናል። እናንተም በጸሎታችሁ ደግፉን፤ በብዙዎች ጸሎት ስለ ተሰጠን ስጦታ ብዙ ሰዎች ስለ እኛ ምስጋና ያቀርባሉ። እንግዲህ ትምክሕታችን ይህ ነው፤ በዚህ ዓለም በተለይም ከእናንተ ጋራ ባለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር በሆነ ቅድስናና ቅንነት እንደ ኖርን ኅሊናችን ይመሰክራል፤ ይህም በሰው ጥበብ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ልታነብቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን ነገር አንጽፍላችሁም፤ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንደምንመካ አሁን የተረዳችሁን በከፊል ቢሆንም፣ በጌታ ኢየሱስ ቀን ሁሉን ትረዳላችሁ።
2 ቆሮንቶስ 1:8-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞች ሆይ! በእስያ ክፍለ ሀገር በነበርንበት ጊዜ የደረሰብንን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ ይህም የደረሰብን መከራ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ወድቆብን ስለ ነበር በሕይወት ለመኖር የነበረን ተስፋ እንኳ ተቋርጦ ነበር። እንዲያውም ሞት እንደ ተፈረደብን ያኽል ተሰምቶን ነበር፤ ይህም ሁሉ የደረሰብን፥ የምንተማመነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ኀይል አለመሆኑን እንድንገነዘብ ነው። ስለዚህ እርሱ ለሞት ከሚያደርስ አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ደግሞም እንደሚያድነን ተስፋችን በእርሱ ነው። እናንተም እኛን በጸሎት ልትረዱን ይገባል፤ በብዙ ጸሎት እኛ የእግዚአብሔርን ርዳታ ስናገኝ ብዙ ሰዎች ደግሞ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም። አንብባችሁ ማስተዋል የምትችሉትን ነገር ካልሆነ ሌላ ምንም አንጽፍላችሁም፤ በሙሉ ማስተዋል እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አሁን ስለ እኛ የምታውቁት በከፊል ነው፤ በኋላ ግን በሙላት እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚህም ምክንያት ጌታ ኢየሱስ በሚመጣበት ቀን እኛ በእናንተ እንደምንመካ እናንተም በእኛ ትመካላችሁ።
2 ቆሮንቶስ 1:8-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን ሆይ፥ በእስያ መከራ እንደ ተቀበልን ልታውቁ እወዳለሁ፤ ለሕይወታችን ተስፋ እስክንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ እጅግ መከራ ጸንቶብን ነበርና። ሙታንን በሚያስነሣቸው በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን በውስጣችን ለመሞት ቈርጠን ነበር። እርሱም እንዲህ ካለ ሞት አዳነን፤ ያድነንማል፤ አሁንም እንደሚያድነን እርሱን እንታመናለን። በብዙዎች ጸሎት ጸጋን እናገኝ ዘንድ፥ ብዙዎችም በእኛ ፋንታ ያመሰግኑ ዘንድ እናንተ በጸሎታችሁ ርዱን። በእግዚአብሔር ቸርነትና ይቅርታ መመኪያችንና የነፃነታችን ምስክር ይህቺ ናትና፥ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ በዚህ ዓለም፥ ይልቁንም በእናንተ ዘንድ ተመላለስን። የምታነቡትንና የምታውቁትን ነው እንጂ፥ ሌላ የምንጽፍላችሁ የለምና፥ ይህንም እስከ ፍጻሜ እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ። እኛ መመኪያችሁ እንደሆን፥ እንዲሁ እናንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን መመኪያችን እንድትሆኑ በከፊል እንዳወቃችሁ ተስፋ እናደርጋለን።
2 ቆሮንቶስ 1:8-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል። ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው። ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንጽፍላችሁምና፤ በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ ደግሞ ትምክህታችን እንደምትሆኑ እንዲሁ ትምክህታችሁ እንድንሆን፥ በከፊል ስለ እኛ እንዳስተዋላችሁ ፈጽማችሁ ታስተውሉት ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ።
2 ቆሮንቶስ 1:8-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን ብታውቁት እንወዳለን፤ በሕይወታችን ተስፋ እስክመቁረጥ የሚያደርስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር። በእርግጥም፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ የሞት ፍርድ እንደተላለፈብን በውስጣችን ተሰምቶን ነበር። እርሱ እንዲህ ካለው የሞት አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ወደፊትም ደግሞ እንደሚያድነን ተስፋችንን በእርሱ ላይ ጥለናል። እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ ስትደግፉን፤ በብዙዎች ጸሎት ስለ ተሰጠን ስጦታ ብዙ ሰዎች ስለ እኛ ምስጋና ያቀርባሉ። ትምክህታችን ይህ ነው፦ በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ባልሆነ፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት እንደኖርን፥ የሕሊናችን ምስክርነት ነው። ልታነብቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን የተለየ ነገር አንጽፍላችሁም፥ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። እኛን በከፊል እንደተረዳችሁን፥ በጌታ ቀን እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንመካለን።