2 ቆሮንቶስ 1:12-16
2 ቆሮንቶስ 1:12-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእግዚአብሔር ቸርነትና ይቅርታ መመኪያችንና የነፃነታችን ምስክር ይህቺ ናትና፥ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ በዚህ ዓለም፥ ይልቁንም በእናንተ ዘንድ ተመላለስን። የምታነቡትንና የምታውቁትን ነው እንጂ፥ ሌላ የምንጽፍላችሁ የለምና፥ ይህንም እስከ ፍጻሜ እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ። እኛ መመኪያችሁ እንደሆን፥ እንዲሁ እናንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን መመኪያችን እንድትሆኑ በከፊል እንዳወቃችሁ ተስፋ እናደርጋለን። በዚህም ታምኜ ጸጋን በዕጥፍ እንድታገኙ በመጀመሪያ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ መከርሁ። በእናንተም በኩል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ፥ ዳግመኛም ከመቄዶንያ እንድመለስና እናንተም ደግሞ ወደ ይሁዳ ሀገር ትሸኙኝ ዘንድ መከርሁ።
2 ቆሮንቶስ 1:12-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ትምክሕታችን ይህ ነው፤ በዚህ ዓለም በተለይም ከእናንተ ጋር ባለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር በሆነ ቅድስናና ቅንነት እንደ ኖርን ኅሊናችን ይመሰክራል፤ ይህም በሰው ጥበብ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ልታነብቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን ነገር አንጽፍላችሁም፤ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንደምንመካ አሁን የተረዳችሁን በከፊል ቢሆንም፣ በጌታ ኢየሱስ ቀን ሁሉን ትረዳላችሁ። በዚህ ርግጠኛ ስለ ነበርሁ በዕጥፍ እንድትጠቀሙ፣ በመጀመሪያ ልጐበኛችሁ ዐቅጄ ነበር። ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁና ከመቄዶንያም በእናንተ በኩል ተመልሼ ወደ ይሁዳ ስሄድ በጕዞዬ እንድትረዱኝ ዐቅጄ ነበር።
2 ቆሮንቶስ 1:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው። ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንጽፍላችሁምና፤ በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ ደግሞ ትምክህታችን እንደምትሆኑ እንዲሁ ትምክህታችሁ እንድንሆን፥ በከፊል ስለ እኛ እንዳስተዋላችሁ ፈጽማችሁ ታስተውሉት ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህም ታምኜ፥ ሁለተኛ ጸጋ ታገኙ ዘንድ አስቀድሜ ወደ እናንተ እንድመጣ፥ በእናንተም መካከል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ።
2 ቆሮንቶስ 1:12-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም። አንብባችሁ ማስተዋል የምትችሉትን ነገር ካልሆነ ሌላ ምንም አንጽፍላችሁም፤ በሙሉ ማስተዋል እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አሁን ስለ እኛ የምታውቁት በከፊል ነው፤ በኋላ ግን በሙላት እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚህም ምክንያት ጌታ ኢየሱስ በሚመጣበት ቀን እኛ በእናንተ እንደምንመካ እናንተም በእኛ ትመካላችሁ። በዚህ ነገር እርግጠኛ ስለ ነበርኩ ሁለት ጊዜ እንድትጠቀሙ ብዬ እናንተን በመጀመሪያ ለመጐብኘት ዐቅጄ ነበር፤ ልጐበኛችሁ ያቀድኩትም ወደ መቄዶንያ ሳልፍና ከዚያም በምመለስበት ጊዜ ነበር፤ በዚህም ሁኔታ ወደ ይሁዳ ምድር በማደርገው ጒዞዬ ትረዱኛላችሁ ብዬ አስቤ ነበር።
2 ቆሮንቶስ 1:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ትምክህታችን ይህ ነው፦ በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ባልሆነ፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት እንደኖርን፥ የሕሊናችን ምስክርነት ነው። ልታነብቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን የተለየ ነገር አንጽፍላችሁም፥ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። እኛን በከፊል እንደተረዳችሁን፥ በጌታ ቀን እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንመካለን። በዚህም እርግጠኛ ስለነበርኩ፥ በእጥፍ እንድትጠቀሙ አስቀድሜ ወደ እናንተ መምጣት ፈልጌ ነበር። ወደ መቄዶንያ ስሄድ በእናንተ በኩል አድርጌ ልጐበኛችሁና፥ ከመቄዶንያም በእናንተ በኩል ተመልሼ ወደ ይሁዳ እንድትልኩኝ ዐቅጄ ነበር።