2 ዜና መዋዕል 7:11-16
2 ዜና መዋዕል 7:11-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት፥ በእግዚአብሔር ቤትና በራሱ ቤት ይሠራው ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ ጨረሰ፤ አከናወነም። እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው፥ “ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም የሚያፈራውን እንጨት ሁሉ ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኀጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖች ይገለጣሉ፤ ጆሮዎችም ያዳምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘለዓለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዐይኖችና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።
2 ዜና መዋዕል 7:11-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ጨረሰ፤ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ያደርግ ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንም ስፍራ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ። “ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣ በማዝበት ጊዜ፣ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር በምሰድድበት ጊዜ፣ በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ወደሚጸለየው ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ያዳምጣሉ። ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ፤ ቀድሼዋለሁም። ዐይኖቼም ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።
2 ዜና መዋዕል 7:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ጨረሰ፤ በእግዚአብሔር ቤትና በራሱ ቤት ይሠራው ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ አከናወነ። እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።
2 ዜና መዋዕል 7:11-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሥ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ሁሉ ባቀደው መሠረት በተሳካ ሁኔታ ከፈጸመ በኋላ፥ እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፤ ይህን ቤተ መቅደስ ለእኔ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስፍራ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ፥ ወይም ሰብሉን እንዲበላ አንበጣ በምልክበት ጊዜ፥ ወይም ቸነፈር በሕዝቤ ላይ በማወርድበት ጊዜ ሁሉ፥ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ እስራኤላውያን ራሳቸውን አዋርደው ከሚያደርጉት ክፉ ነገር በመራቅ ተጸጽተውና ንስሓ ገብተው ወደ እኔ ቢጸልዩ በሰማይ ሆኜ እሰማቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ምድራቸውም እንደገና ፍሬያማ እንድትሆን አደርጋለሁ፤ ይህን ቤተ መቅደስ እጠብቀዋለሁ፤ በዚህ ቤተ መቅደስ የሚቀርበውንም ጸሎት ሁሉ እሰማለሁ። ለዘለዓለም የስሜ መጠሪያ ይሆን ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጬዋለሁ ቀድሼዋለሁም፤ በልቤም ውስጥ አድርጌ ዘወትር እጠብቀዋለሁ።
2 ዜና መዋዕል 7:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሰሎሞንም የጌታን ቤትና የንጉሡን ቤት ጨረሰ፤ በጌታ ቤትና በራሱ ቤት ለመሥራት በልቡ ያሰበውን ሁሉ አከናወነ። ጌታም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ራሳቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘለዓለም በዚያ እንዲኖር ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም፤ ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።