ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 7
7
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
(1ነገ. 8፥62-66)
1ንጉሥ ሰሎሞን ጸሎቱን እንደ ፈጸመ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውንና ሌላውን መሥዋዕት በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው፤ #ዘሌ. 9፥23-24። 2ቤተ መቅደሱ በእግዚአብሔር ክብር ስለ ተሞላ ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት አልቻሉም። 3እስራኤላውያን እሳት ከሰማይ ሲወርድና የእግዚአብሔርም ክብር በቤተ መቅደስ ላይ ማረፉን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው፦
“እግዚአብሔር ቸር ነው፤
ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ነው!”
እያሉ ሰገዱ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ። #1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 107፥1፤ 118፥1፤ 136፥1፤ ኤር. 33፥11። 4ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞንና በዚያ የነበረው ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ፤ 5ሰሎሞንም ኻያ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶችና አንድ መቶ ኻያ ሺህ በጎችን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ በዚህም ዐይነት ንጉሥ ሰሎሞንና ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረጉ። 6ካህናቱም በተመደበላቸው ቦታ ቆሙ፤ ከእነርሱም ፊት ለፊት ሌዋውያን ቆመው አስቀድሞ ንጉሥ ዳዊት አሠርቶ እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጠቀምባቸው በነበሩት የዜማ መሣሪያዎች ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በመዘመር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ካህናቱም መለከት ሲነፉ እስራኤላውያን ሁሉ ቆመው ነበር።
7እንዲሁም ሰሎሞን ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን አደባባይ መካከለኛ ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረገ፤ ቀጥሎም በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህል መባና የኅብረት መሥዋዕት፥ የእንስሶች ስብ ሁሉ በዚያ ስፍራ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከነሐስ ያሠራው መሠዊያ ይህን ሁሉ መሥዋዕት መያዝ ስለማይችል ነው።
8በዚያም በቤተ መቅደሱ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ሰባት ቀን ሙሉ የዳስ በዓል አክብረው ሰነበቱ፤ በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ሸለቆ ድረስ ካለው ምድር ሁሉ የመጣው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነበር። 9መሠዊያውን ለእግዚአብሔር የተለየ በማድረግ ሥነ ሥርዓት ላይ ሰባት ቀን አሳለፉ፤ ሌላ ሰባት ቀን በዓሉን በማክበር ከሰነበቱ በኋላ በስምንተኛው ቀን የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ተደርጎ የበዓሉ ፍጻሜ ሆነ፤ 10በማግስቱ ማለትም በሰባተኛው ወር በሃያ ሦስተኛው ቀን ሰሎሞን፥ ወደሚኖሩበት ስፍራ እንዲሄዱ ሰዎቹን አሰናበተ፤ እነርሱም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤል፥ ለዳዊትና ለሰሎሞን ስለ ሰጠው በረከት ተደስተው ወደየመኖሪያ ስፍራቸው ሄዱ።
እግዚአብሔር ለሰሎሞን እንደገና መገለጡ
(1ነገ. 9፥1-9)
11ንጉሥ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ሁሉ ባቀደው መሠረት በተሳካ ሁኔታ ከፈጸመ በኋላ፥ 12እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፤ ይህን ቤተ መቅደስ ለእኔ መሥዋዕት የሚቀርብበት ስፍራ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ፤ 13ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ፥ ወይም ሰብሉን እንዲበላ አንበጣ በምልክበት ጊዜ፥ ወይም ቸነፈር በሕዝቤ ላይ በማወርድበት ጊዜ ሁሉ፥ 14በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ እስራኤላውያን ራሳቸውን አዋርደው ከሚያደርጉት ክፉ ነገር በመራቅ ተጸጽተውና ንስሓ ገብተው ወደ እኔ ቢጸልዩ በሰማይ ሆኜ እሰማቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ምድራቸውም እንደገና ፍሬያማ እንድትሆን አደርጋለሁ፤ 15ይህን ቤተ መቅደስ እጠብቀዋለሁ፤ በዚህ ቤተ መቅደስ የሚቀርበውንም ጸሎት ሁሉ እሰማለሁ። 16ለዘለዓለም የስሜ መጠሪያ ይሆን ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጬዋለሁ ቀድሼዋለሁም፤ በልቤም ውስጥ አድርጌ ዘወትር እጠብቀዋለሁ። 17አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ አንተም በታማኝነት ብታገለግለኝ፥ ሕጎቼንና ሥርዓቴን በመጠበቅ ትእዛዞቼን ሁሉ ብትፈጽም፥ 18ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘርህ መካከል በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ዘወትር ይኖራል’ ስል በሰጠሁት የተስፋ ቃል መሠረት መንግሥትህን አጸናለሁ፤ #1ነገ. 2፥4። 19ነገር ግን አንተና ሕዝብህ እኔ የሰጠኋችሁን ሕጎችና ትእዛዞች ባትጠብቁ፥ ባዕዳን አማልክትንም ብታመልኩና፥ ብትሰግዱላቸው፥ 20እኔ ከሰጠኋችሁ ከምድሬ ተነቅላችሁ እንድትባረሩ አደርጋለሁ፤ እኔ ለስሜ የቀደስኩትን ይህን ቤተ መቅደስ እተወዋለሁ፤ በሁሉ ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦችም በንቀት መሳለቂያና መዘባበቻ ያደርጉታል።
21“ይህ ቤተ መቅደስ እነሆ አሁን ከፍ ያለ ክብር አለው፤ በዚያን ጊዜ ግን በቤተ መቅደሱ አጠገብ የሚያልፍ ሰው ሁሉ በመገረም ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ ስለምን እንደዚህ አደረገ?’ ብሎ ይጠይቃል፤ 22ሰዎችም ‘እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ጥፋት በእነርሱ ላይ ያደረሰባቸው ከግብጽ ያወጣቸውን የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉና ስለ ሰገዱላቸው ነው’ ሲሉ ይመልሱላቸዋል።”
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997