ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 6

6
ሰሎሞን ለሕዝቡ የተናገረው ቃል
(1ነገ. 8፥12-21)
1ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሔር ሆይ፥ ‘በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ’ ብለሃል፤
2እነሆ እኔ ግርማ ያለው ውብ ቤተ መቅደስ
ለአንተ ሠርቼአለሁ፤
ይህም ቤተ መቅደስ አንተ ለዘለዓለም
የምትኖርበት ስፍራ ይሆናል።”
3በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በዚያ ቆመው ነበር፤ ንጉሥ ሰሎሞንም ወደ እነርሱ ፊቱን መልሶ፥ የእግዚአብሔር በረከት በእነርሱ ላይ እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ 4“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! እርሱ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠውን የተስፋ ቃል ፈጽሞአል፤ የሰጠውም የተስፋ ቃል እንዲህ የሚል ነው፦ 5‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራበት ስፍራ ከመላው የእስራኤል ምድር አንድም ከተማ፥ እንዲሁም ሕዝቤን እስራኤልን የሚመራ ማንንም ሰው አልመረጥኩም ነበር፤ 6አሁን ግን ስሜ እንዲጠራበት ኢየሩሳሌምን፥ ሕዝቤን እንድትመራም አንተን ዳዊትን መርጬአለሁ።’ ”
7ቀጥሎም ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “አባቴ ዳዊት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስቦ ነበር፤ 8እግዚአብሔር ግን ‘ለእኔ ቤተ መቅደስን ለመሥራት በመፈለግህ መልካም አድርገሃል፤ 9ሆኖም ለስሜ መጠሪያ እንዲሆን ቤተ መቅደስን የሚሠራልኝ ከአብራክህ የተገኘ የአንተው የራስህ ልጅ እንጂ አንተ አይደለህም’ አለው።” #2ሳሙ. 7፥1-13፤ 1ዜ.መ. 17፥1-12።
10“እነሆ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ፈጽሞአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ እግር ተተክቼ የእስራኤል ንጉሥ ሆኜአለሁ፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ሠርቼአለሁ፤ 11እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦትም በቤተ መቅደሱ ውስጥ አኑሬአለሁ።”
ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት
(1ነገ. 8፥22-53)
12-13ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሕዝቡ ባለበት በመሠዊያው ፊት ለፊት፥ በአደባባዩ መካከል በሚገኘው መድረክ ላይ ወጥቶ ቆመ። ስፋቱና ርዝመቱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሴንቲ ሜትር፥ ቁመቱ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር የሆነ መድረክ ከነሐስ አሠርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፤ እርሱም ሕዝቡ ሁሉ ሊያዩት በሚችሉበት በዚህ መድረክ ላይ በመንበርከክ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ እንዲህ ሲል ጸለየ። 14“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! በሰማይም ሆነ በምድር ሁሉ እንደ አንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤ አንተ ከሕዝብህ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን ትጠብቃለህ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ለሚሄዱ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ትገልጥላቸዋለህ። 15ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አጽንተሃል፤ የተናገርከው እያንዳንዱ የተስፋ ቃልም እነሆ ዛሬ ተፈጽሞአል፤ 16የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ ሕጌን በጥንቃቄ እንደ ጠበቅህ ልጆችህም ቢጠብቁ፥ ከዘርህ መካከል በእስራኤል ላይ በፊቴ የሚነግሥ ዘወትር ይኖራል’ በማለት የገባህለትን ቃል ኪዳን አሁን እንድታጸናልኝ እለምንሃለሁ፤ #1ነገ. 2፥4። 17እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአገልጋይህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግልኝ።
18“ነገር ግን በእውነት እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሰዎች ጋር ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ፥ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤትማ ምንኛ ያንስ? #2ዜ.መ. 2፥6። 19ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፥ ወደ እኔ ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ በፊትህም የምጸልየውን ጸሎትና ጥሪ አዳምጥ። 20‘ስሜ ይጠራበታል’ ወዳልከው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቀንና ሌሊት ተመልከት፤ እኔም አገልጋይህ ወደዚህ ቤተ መቅደስ የምጸልየውን ጸሎት ስማ፤ #ዘዳ. 12፥11። 21እኔም አገልጋይህ ሆንኩ ሕዝብህ እስራኤል ፊታችንን ወደዚህ ስፍራ መልሰን ስንጸልይ ጸሎታችንን ስማ፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማን፤ ይቅር በለንም።
22“አንድ ሰው ባልንጀራውን መበደሉን የሚገልጥ ክስ ቀርቦበት በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው መሠዊያ አምጥተውት ከበደል ንጹሕ መሆኑን በመሐላ በሚያረጋግጥበት ጊዜ፥ 23እግዚአብሔር ሆይ፥ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ ይኸውም በደል የሠራውን ሰው በጥፋቱ መጠን እንዲቀጣ፥ ንጹሑም ነጻ እንዲወጣ አድርግ።
24“ሕዝብህ እስራኤል ኃጢአት ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ድል ሲሆኑ ተጸጽተው ወደ አንተ በመመለስ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢመጡና የአንተን ይቅርታ ለማግኘት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በትሕትና ቢለምኑህ፥ 25አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የሕዝብህንም ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸውና ለእነርሱ ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሰህ አግባቸው።
26“ሕዝብህ በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው በምታደርግበት ጊዜ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥ 27እግዚአብሔር ሆይ፥ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ አገልጋዮችህ የሆኑትን የእስራኤል ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል፤ ቅን የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ አስተምራቸው፤ እግዚአብሔር ሆይ ለዘለቄታው ርስታቸው ይሆን ዘንድ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው በዚህች ምድር ላይ ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ።
28“በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት ጊዜ፥ እንዲሁም የእህል ሰብል በሚያቃጥል ነፋስና በአንበጣ መንጋ በሚወድምበት ጊዜ፥ ወይም ጠላቶቻቸው በሕዝብህ ላይ ከበባ በሚያደርጉበት ጊዜ፥ ወይም በሕዝብህ ላይ ልዩ ልዩ በሽታና ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፥ 29በሕዝብህ በእስራኤል መካከል ልብን የሚሰብር መሪር ሐዘን ደርሶባቸው እጃቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥ 30ጸሎታቸውን ስማ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት በደላቸውን ይቅር በላቸው፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው። 31በዚህም ዐይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች ሆነው እንዲያከብሩህ አድርግ።
32“በሩቅ አገር የሚኖር የውጪ አገር ሰው የስምህን ገናናነትና ለሕዝብህ ያደረግኸውን ድንቅ ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ በዚህ ቤተ መቅደስ ሊያመልክህና ሊጸልይ ቢመጣ፥ 33አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤል እንደሚያደርገው በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ ታዛዦች እንዲሆኑልህ፥ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህን ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት ስፍራ መሆኑን ያውቃሉ።
34“ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥ 35ጸሎታቸውን ስማ፤ በሰማይ ሆነህ ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ።
36“መቼም በደል የማይሠራ ሰው የለምና ሕዝብህ እስራኤላውያን ኃጢአት በመሥራት አንተን ቢያሳዝኑህ፥ አንተም ተቈጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ያ አገር ሩቅ ቢሆንም እንኳ፥ 37ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩበት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ እግዚአብሔር ሆይ፥ ጸሎታቸውን ስማ፤ 38ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለስምህ ወደሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥ 39ጸሎታቸውን ስማ፤ በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማትም ምሕረት አድርግላቸው፤ የሕዝብህን ኃጢአት ሁሉ ይቅር በል።
40“አምላኬ ሆይ፥ በዚህ ስፍራ ወደሚቀርበው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ ጆሮዎችህም አጣርተው የሚያደምጡ እንዲሆኑ እለምንሃለሁ። 41እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ አሁን ተነሥተህ ከኀያሉ ታቦትህ ጋር ወደ ማረፊያ ቦታህ ና፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ታማኞችህም በበረከትህ ይደሰቱ፤ 42እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ የቀባኸውን ንጉሥ አትተወው፤ ለአገልጋይህ ለዳዊት ያደረግህለትን ፍቅር አስታውስ።” #መዝ. 132፥8-10።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ