2 ዜና መዋዕል 20:20-30
2 ዜና መዋዕል 20:20-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው። ከሕዝቡም ጋራ ከተመካከረ በኋላ ከሰራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ። መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም። የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ። የይሁዳ ሰዎች ምድረ በዳውን ቍልቍል ወደሚያሳየው ቦታ መጥተው ግዙፉን ሰራዊት ሲመለከቱ፣ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤ አንድም ሰው አላመለጠም። ኢዮሣፍጥና ሰዎቹም ምርኳቸውን ለማጋዝ ሄዱ፤ በዚያም መካከል እጅግ ብዙ መሣሪያና ልብስ፣ ሊሸከሙ ከሚችሉትም በላይ ውድ ዕቃዎችን አገኙ። ምርኮውም ከመብዛቱ የተነሣ ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀ። በአራተኛውም ቀን እግዚአብሔርን ባመሰገኑበት በበረከት ሸለቆ ተሰበሰቡ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተብሎ የተጠራው ከዚህ የተነሣ ነው። እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ በኢዮሣፍጥ እየተመሩ፣ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ገቡም በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ። እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋቸው በሰሙ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ወደቀባቸው። አምላኩ በየአቅጣጫው ዕረፍት ስለ ሰጠው፣ የኢዮሣፍጥ መንግሥት ሰላም አግኝቶ ነበር።
2 ዜና መዋዕል 20:20-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፥ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢዩም እመኑ፤ ነገሩም ይቀናላችኋል” አለ። ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፥ “ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” የሚሉትንም፥ በቅድስና የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ኀይልን ሰጣቸው፤ እነርሱም ተመቱ። የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ፥ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እርስ በርሳቸው ሊጠፋፉ ተነሡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳው መጠበቂያ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፤ ያመለጠም ሰው አልነበረም። ኢዮሳፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ፤ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፤ ማረኩትም፤ ምርኮውም ብዙ ነበርና ምርኮውን እየሰበሰቡ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቈዩ። በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፤ በዚያም እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ ንጉሣቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በበገናና በመሰንቆ፥ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ቤት ገቡ። እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሀት ሆነ። የኢዮሣፍጥም መንግሥት ሰላም ሆነች፤ አምላኩም እግዚአብሔር በዙሪያው ካሉ አሳረፈው።
2 ዜና መዋዕል 20:20-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው። ከሕዝቡም ጋራ ከተመካከረ በኋላ ከሰራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ። መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም። የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ። የይሁዳ ሰዎች ምድረ በዳውን ቍልቍል ወደሚያሳየው ቦታ መጥተው ግዙፉን ሰራዊት ሲመለከቱ፣ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤ አንድም ሰው አላመለጠም። ኢዮሣፍጥና ሰዎቹም ምርኳቸውን ለማጋዝ ሄዱ፤ በዚያም መካከል እጅግ ብዙ መሣሪያና ልብስ፣ ሊሸከሙ ከሚችሉትም በላይ ውድ ዕቃዎችን አገኙ። ምርኮውም ከመብዛቱ የተነሣ ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀ። በአራተኛውም ቀን እግዚአብሔርን ባመሰገኑበት በበረከት ሸለቆ ተሰበሰቡ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተብሎ የተጠራው ከዚህ የተነሣ ነው። እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ በኢዮሣፍጥ እየተመሩ፣ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ገቡም በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ። እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋቸው በሰሙ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ወደቀባቸው። አምላኩ በየአቅጣጫው ዕረፍት ስለ ሰጠው፣ የኢዮሣፍጥ መንግሥት ሰላም አግኝቶ ነበር።
2 ዜና መዋዕል 20:20-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፤ ነገሩም ይሰላላችኋል” አለ። ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚሉትን፥ ጌጠኛ ልብስ ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩትን መዘምራንን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ። የአሞንና የሞዓብም ልጆችም በሴይርም ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፤ ያመለጠም ሰው አልነበረም። ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ፤ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃ፥ ልብስ፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፤ በዘበዙትም፤ ሁሉንም ይሸከሙ ዘንድ አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር። በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፤ በዚያም እግዚአብሔርን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ ተመለሱ። በበገናና በመሰንቆ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ቤት ገቡ። እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሃት ሆነ። የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጥ አለች፤ አምላኩም በዙሪያው ካሉ አሳረፈው።
2 ዜና መዋዕል 20:20-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰዎቹ በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ተቆዓ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓማ አገር ሄዱ፤ ወደዚያ ለመሄድ ጒዞ በመጀመር ላይ ሳሉም ኢዮሣፍጥ እነርሱን “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱም ብርታትን ይሰጣችኋል፤ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩአችሁንም እመኑ፤ ይሳካላችኋልም” አላቸው። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከሕዝቡ ጋር ከተመካከረ በኋላ መዘምራኑ በተቀደሱ በዓላት የሚለብሱአቸውን ካባዎች ለብሰው “ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በመዘመር በሠራዊቱ ፊት ለፊት እንዲያልፉ አዘዘ። መዘምራኑ መዘመርና ማመስገን በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር በወራሪዎቹ ሠራዊት ላይ ድብቅ ጦር አምጥቶባቸው፥ ግራ ተጋቡ፤ ስለዚህ ዐሞናውያንና ሞአባውያን በኤዶማውያን ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው በሙሉ ደመሰሱአቸው፤ ከዚያም በመቀጠል በጭካኔ እርስ በርሳቸው ተፋጁ፤ የይሁዳ ሠራዊት በረሓውን የሚያሳይ ከፍተኛ ቦታ በደረሱ ጊዜ ጠላቶቹ ወዳሉበት አቅጣጫ ሲመለከቱ ጠላቶቹ በሙሉ አልቀው ሬሳዎቻቸው በምድር ላይ ተጋድመው አዩ፤ አንድም እንኳ በሕይወት ተርፎ ያመለጠ አልነበረም። ከዚህ በኋላ ኢዮሣፍጥና ወታደሮቹ ምርኮ ለመውሰድ ወደዚያ ሄዱ፤ ብዙ የቀንድ ከብት፥ ስንቅና ትጥቅ፥ ልብስና ሌላም ውድ የሆኑ ዕቃዎች አገኙ፤ ምርኮውንም ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀባቸው፤ ነገር ግን ምርኮው እጅግ ብዙ ስለ ነበር ሁሉንም መውሰድ አልቻሉም፤ በአራተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ “የበረከት ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ተሰበሰቡ፤ እግዚአብሔር ስላደረገላቸውም ነገር ሁሉ አመሰገኑት፤ ሸለቆው “በረከት” ተብሎ የተጠራውም ስለዚህ ነው። ከዚያ በኋላ በኢዮሣፍጥ መሪነት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ድልን ስላጐናጸፋቸው እየተደሰቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም በእምቢልታ፥ በዋሽንትና በበገና ድምፅ እየታጀቡ በሰልፍ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋ የሰሙ መንግሥታት ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርሀትና ድንጋጤ ዐደረባቸው። ስለዚህም ኢዮሣፍጥ አገሪቱን በሰላም አስተዳደረ፤ እግዚአብሔርም በሁሉ አቅጣጫ የሰላም ዋስትና ሰጠው።
2 ዜና መዋዕል 20:20-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ማልደውም በመነሣት ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና እንዲህ አለ፦ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በጌታ እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሳካላችኋል።” ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፦ “ጽኑ ፍቅሩ ለዘዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ” የሚሉትንም ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለጌታም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሙዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ ጌታ ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተሸነፉ። የአሞንና የሞዓብም ልጆችም በሴይርም ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ሊገድሉአቸውና ሊያጠፉአቸውም ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ አንዱ ሌላውን በማገዝ እርስ በርስ ተጠፋፉ። የይሁዳም ሰዎች በምድረ በዳ ወዳለው የመጠበቅያ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፥ ያመለጠም ሰው አልነበረም። ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ለመውሰድ መጡ፤ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፥ በዘበዙትም፥ ሁሉንም ለመሸከም አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር። በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፥ በዚያም ጌታን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ ጌታ በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ። በበገናና በመሰንቆ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ጌታ ቤት ገቡ። ጌታ የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የጌታር ፍርሃት አደረባቸው። የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጠጥታ ሰፈነበት፥ አምላኩም በዙርያው ካሉ አሳረፈው።