ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፥ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢዩም እመኑ፤ ነገሩም ይቀናላችኋል” አለ። ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፥ “ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” የሚሉትንም፥ በቅድስና የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ኀይልን ሰጣቸው፤ እነርሱም ተመቱ። የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ፥ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እርስ በርሳቸው ሊጠፋፉ ተነሡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳው መጠበቂያ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፤ ያመለጠም ሰው አልነበረም። ኢዮሳፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ፤ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፤ ማረኩትም፤ ምርኮውም ብዙ ነበርና ምርኮውን እየሰበሰቡ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቈዩ። በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፤ በዚያም እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ ንጉሣቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በበገናና በመሰንቆ፥ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ቤት ገቡ። እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሀት ሆነ። የኢዮሣፍጥም መንግሥት ሰላም ሆነች፤ አምላኩም እግዚአብሔር በዙሪያው ካሉ አሳረፈው።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 20 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 20:20-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች