መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 20
20
1እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መጡ። 2ሰዎችም መጥተው፥ “ከባሕሩ ማዶ ከሶርያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም፥ ዓይንጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ናቸው” ብለው ለኢዮሣፍጥ ነገሩት። 3ኢዮሣፍጥም ፈራ፤ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ። 4ይሁዳም እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ተሰበሰበ፤ ከይሁዳ ከተሞችም ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ መጡ።
5ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤ 6እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኀይልና ችሎታ በእጅህ ነው፤ ሊቋቋምህም የሚችል የለም። 7አምላካችን ሆይ፥ በዚህ ምድር የነበሩትን አሕዛብ ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት ያሳደድህ፥ ለወዳጅህም ለአብርሃም ዘር ለዘለዓለም የሰጠሃት አንተ አይደለህምን? 8እነርሱ ተቀመጡባት፤ ለስምህም መቅደስን ሠሩባት። 9እንዲህም አሉ፦ ክፉ ነገር፥ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ፥ ቢመጣብን በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ እንቆማለን፤ ስምህ በዚህ ቤት ላይ ነውና፤ በመከራችንም ወደ አንተ እንጮኻለን፥ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ። 10አሁንም እነሆ፥ እስራኤል ከግብዕ ምድር በወጡ ጊዜ ያልፉባቸው ዘንድ ያልፈቀድህላቸው የአሞንና የሞዓብ ልጆች፥ የሴይርም ተራራ ሰዎች እንዳያጠፉአቸው ከእነርሱ ፈቀቅ ብለው ነበር። 11እነሆ፥ አሁን ለወሮታችን ክፋት ይመልሱልናል፤ ከሰጠኸንም ርስት ያወጡን ዘንድ መጥተዋል። 12አምላካችን ሆይ፥ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን መቃወም እንችል ዘንድ ኀይል የለንም፤ የምናደርግባቸውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዐይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው።” 13የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸው፥ ከልጆቻቸውም ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር።
14የእግዚአብሔርም መንፈስ ከአሳፍ ወገን በነበረው በሌዋዊው በምታንያስ ልጅ በኢያሔል ልጅ በብልአንያ ልጅ በዘካርያስ ልጅ በኡዝሔል ላይ በጉባኤው መካከል መጣ፤ 15እንዲህም አለ፥ “ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ! ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፦ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 16ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በአሲስ ዐቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በኢያርሔል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። 17እናንተ የምቷጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፤ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገም ውጡባቸው።” 18ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ሰገደ፤ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። 19ሌዋውያንም፥ ከቀዓት ልጆችና ከቆሬ ልጆች የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ከፍ ባለ ታላቅ ድምፅ ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።
20ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፥ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢዩም እመኑ፤ ነገሩም ይቀናላችኋል” አለ። 21ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፥ “ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” የሚሉትንም፥ በቅድስና የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። 22ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ኀይልን ሰጣቸው፤ እነርሱም ተመቱ። 23የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ፥ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እርስ በርሳቸው ሊጠፋፉ ተነሡ።
24የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳው መጠበቂያ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፤ ያመለጠም ሰው አልነበረም። 25ኢዮሳፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ፤ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፤ ማረኩትም፤ ምርኮውም ብዙ ነበርና ምርኮውን እየሰበሰቡ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቈዩ። 26በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፤ በዚያም እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። 27የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ ንጉሣቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 28በበገናና በመሰንቆ፥ በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ቤት ገቡ። 29እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሀት ሆነ። 30የኢዮሣፍጥም መንግሥት ሰላም ሆነች፤ አምላኩም እግዚአብሔር በዙሪያው ካሉ አሳረፈው።
31ኢዮሣፍጥም በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሠላሳ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሳሊ ልጅ አዙባ ነበረች። 32በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን የሆነውን ነገር ከማድረግ ፈቀቅ አላለም። 33ነገር ግን ኮረብታዎች ገና በዚያ ነበሩ፤ ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር አላቀኑም ነበር። 34የቀረውም የፊተኞቹና የኋለኞቹ የኢዮሣፍጥ ነገሮች፥ እነሆ የእስራኤልን ነገሥታት ታሪክ በጻፈው በአናኒ ልጅ በነቢዩ በኢዩ ታሪክ ተጽፈዋል።
35ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ፤ ይህም በደልን የሠራ ነበር፦ 36ወደ ተርሴስም የሚሄዱትን መርከቦች ያሠራ ዘንድ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነ፤ መርከቦቹንም በጋሲዮንጋብር አሠሩ። 37የማርሶስ ሰው የኢያድያ ልጅ አልዓዛር፥ “ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና እግዚአብሔር ሥራህን አፍርሶታል” ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፤ ወደ ተርሴስም ይሄዱ ዘንድ አልቻሉም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 20: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ