መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 21
21
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም
(2ነገ. 8፥17-24)
1ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2ለእርሱም የኢዮሣፍጥ ልጆች አዛርያስ፥ ኢይሔል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤል፥ ሰፋጥያስ የሚባሉ ስድስት ወንድሞች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። 3አባታቸውም ብዙ ስጦታ፥ ብርና ወርቅ፥ የከበረም ዕቃ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሰጣቸው፤ መንግሥቱን ግን የበኵር ልጁ ስለሆነ ለኢዮራም ሰጠው። 4ኢዮራምም በአባቱ መንግሥት ላይ ተነሥቶ በጸና ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉ፥ ሌሎችንም የእስራኤልን መሳፍንት በሰይፍ ገደለ። 5ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። 6የአክዓብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 7ነገር ግን ከዳዊት ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን፥ ለእርሱና ለልጆቹም በዘመናት ሁሉ መብራትን ይሰጠው ዘንድ ስለ ሰጠው ተስፋ እግዚአብሔር የዳዊትን ቤት ያጠፋ ዘንድ አልወደደም።
8በእነዚያም ዘመናት የኤዶምያስ ሰዎች በይሁዳ ላይ ዐመፁ፤ ለራሳቸውም ንጉሥ አነገሡ። 9ኢዮራምም ከአለቆቹና ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስ ሰዎችን መታ፤ ሕዝቡም ወደ ድንኳናቸው ሸሹ። 10ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፀ፤ በዚያም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዐመፀ፤ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና።
11ደግሞም በይሁዳ ተራሮች ላይ መስገጃዎችን ሠራ፤ በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን እንዲያመነዝሩ አደረጋቸው፤ የይሁዳንም ሰዎች አሳታቸው። 12ከነቢዩም ከኤልያስ እንዲህ የሚል ጽሕፈት መጣበት፥ “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ፥ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥ 13በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥ የአክዓብም ቤት እንዳደረገ ይሁዳንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እንዲያመነዝሩ አድርገሃልና፥ ከአንተም የሚሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን ገድለሃልና፥ 14እነሆ፥ እግዚአብሔር ሕዝብህንና ልጆችህን፥ ሚስቶችህንም፥ ያለህንም ንብረት ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይቀሥፋል። 15አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ በየዕለቱ እስኪወጣ ድረስ በክፉ የአንጀት ደዌ ትታመማለህ።”
16እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረብያን ሰዎች በኢዮራም ላይ አስነሣ። 17ወደ ይሁዳም ወጡ፤ በረቱባቸውም፤ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ወንዶች ልጆቹንም፥ ሴቶች ልጆቹንም ወሰዱ፤ ከታናሹም ልጅ ከአካዝያስ በቀር ልጅ አልቀረለትም።
18ከዚህም ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር መድኀኒት በማይገኝለት ደዌ አንጀቱን ቀሠፈው። 19ከቀንም ወደ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀቱ ወጣ፤ በክፉም ደዌ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርገው እንደ ነበረ ለእርሱ የመቃብር ወግ አላደረገም። 20መንገሥም በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ሄደ፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 21: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ