ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20:20-30

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20:20-30 አማ05

ሰዎቹ በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ተቆዓ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓማ አገር ሄዱ፤ ወደዚያ ለመሄድ ጒዞ በመጀመር ላይ ሳሉም ኢዮሣፍጥ እነርሱን “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱም ብርታትን ይሰጣችኋል፤ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩአችሁንም እመኑ፤ ይሳካላችኋልም” አላቸው። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከሕዝቡ ጋር ከተመካከረ በኋላ መዘምራኑ በተቀደሱ በዓላት የሚለብሱአቸውን ካባዎች ለብሰው “ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በመዘመር በሠራዊቱ ፊት ለፊት እንዲያልፉ አዘዘ። መዘምራኑ መዘመርና ማመስገን በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር በወራሪዎቹ ሠራዊት ላይ ድብቅ ጦር አምጥቶባቸው፥ ግራ ተጋቡ፤ ስለዚህ ዐሞናውያንና ሞአባውያን በኤዶማውያን ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው በሙሉ ደመሰሱአቸው፤ ከዚያም በመቀጠል በጭካኔ እርስ በርሳቸው ተፋጁ፤ የይሁዳ ሠራዊት በረሓውን የሚያሳይ ከፍተኛ ቦታ በደረሱ ጊዜ ጠላቶቹ ወዳሉበት አቅጣጫ ሲመለከቱ ጠላቶቹ በሙሉ አልቀው ሬሳዎቻቸው በምድር ላይ ተጋድመው አዩ፤ አንድም እንኳ በሕይወት ተርፎ ያመለጠ አልነበረም። ከዚህ በኋላ ኢዮሣፍጥና ወታደሮቹ ምርኮ ለመውሰድ ወደዚያ ሄዱ፤ ብዙ የቀንድ ከብት፥ ስንቅና ትጥቅ፥ ልብስና ሌላም ውድ የሆኑ ዕቃዎች አገኙ፤ ምርኮውንም ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀባቸው፤ ነገር ግን ምርኮው እጅግ ብዙ ስለ ነበር ሁሉንም መውሰድ አልቻሉም፤ በአራተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ “የበረከት ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ተሰበሰቡ፤ እግዚአብሔር ስላደረገላቸውም ነገር ሁሉ አመሰገኑት፤ ሸለቆው “በረከት” ተብሎ የተጠራውም ስለዚህ ነው። ከዚያ በኋላ በኢዮሣፍጥ መሪነት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ድልን ስላጐናጸፋቸው እየተደሰቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜም በእምቢልታ፥ በዋሽንትና በበገና ድምፅ እየታጀቡ በሰልፍ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋ የሰሙ መንግሥታት ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርሀትና ድንጋጤ ዐደረባቸው። ስለዚህም ኢዮሣፍጥ አገሪቱን በሰላም አስተዳደረ፤ እግዚአብሔርም በሁሉ አቅጣጫ የሰላም ዋስትና ሰጠው።